በክልሉ የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አደረጃጀት ተቋቁሞ ወደሥራ ተገብቷል

52

ባህር ዳር ጥር 9/2011 በክልሉ የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ወቅቱን ያገናዘበ የፀጥታ አደረጃጀት ተቋቁሞ ወደሥራ በመገባቱ ህብረተሳቡ ያለምንም ስጋት በዓሉን ማክበር እንዳለበት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰኢድ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በየደረጃው በድምቀት የሚከበረው  የጥምቀት በዓል ያልምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የፀጥታ መዋቅር አደረጃጀት ተቋቁሞ የቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራ ተሰርቷል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሁለት ቀናት በፊት በየጥምቀት በህሮችና ስርዓቱ በሚከወንባቸው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሉ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመጥን መልኩ የቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ የፀጥታ አካላትና የፌዴራል ፖሊስ  በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ህብረተሰቡ ያለምንም የጸጥታ ስጋት በዓሉን እንደተለመደው በደማቅ ሁኔታ ማክበር እንዳለበት አስታውቀዋል።

በተለይ በዓሉ በተለየ ድምቀት ለሚከበርበት የጎንደር ከተማ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ያስረዱት ረዳት ኮሚሽነሩ "በዓሉን ለማክበር ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚመጡ ቱሪስቶች ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት ሊገባቸው አይገባም" ብለዋል።

ወንጀልን የመከላከል ስራው ህብረተሰቡን በኮሚኒቲ ፖሊሲንግ አማካኝነት ያሳተፈ ከመሆኑ በተጨማሪ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ጠንከራ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።

የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም በበኩላቸው " የባህር ዳር አገረ ስብከት ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችን አደረጃጀት ፈጥራ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ እየሰራች ነው" ብለዋል።

በዓሉ ድህነት የተገኘበት ዕለት መታሰቢያ በመሆኑ መዕመናን ሰላምን አጥብቀው በመዘመርና ሰላምን የሚያውኩትን አጥብቀው በመምከር የሚያከብሩት በዓል መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም