በጋምቤላ ክልል ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው

67

ጋምቤላ ጥር 9/2011 በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እየለማ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የክልሉ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በበጋው ወራት ያለውን ሰፊ የውሃ አማራጭና እርጥበታማ አፈርን በመጠቀም ልማቱን እያከናወኑ ናቸው።

ልማቱን ለማከናወን በተከናወኑ የንቅናቄ ስራዎች  በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ወደ  ልማቱ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

ልማቱ ወንዞች ፣ ኩሬዎችና ሐይቆችን በመጥለፍ፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችንና እርጥበታማ አፈርን በመጠቀም ሥራውን  በማከናወን ላይ  ናቸው።

እየለማ ካለው መሬትም ከ750 ሺህ ኩንታል በላይ የሰብልና የጓሮ አትክልት ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ እየለማ ያለው መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ አለው። ለመሰብሰብ የታቀደው ምርት መጠን በ350ሺህ ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

ሥራውን ለማሳካትም የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

በሥራው 40 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ወለጋ ኡሉክ እንደሚሉት በበጋው ወራት 28 ሺህ ሄክታር በበቆሎ፣ በቲማቲም፣ በኡክራ/ በአሙላ/ና በሌሎች ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።

ቀሪውን መሬትም ወደ ልማት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ በመስኖ ልማት የተሰማሩት አቶ አቡላ ዳንጉር በአቅራቢያቸው ያለውን ውሃ በጄኔሬተር በመሳብ በዓመት  ሁለት ጊዜ በማልማት ተጠቀሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት በቲማቲምና በኡክራ/ በአሙላ/ በማልማት ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል የባሮ፣ የአሌሮ፣ የአኮቦ፣ የጊሎ ወንዞችንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም 780 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም