በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተቋረጠ

90

አዳማ ጥር 9/2011 በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደት መቋረጡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገለጹ።

የዪኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ለኢዜአ እንደተናገሩት የተቋሙ ተማሪዎች ወጣ ገባ በማለት የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስተጓጎል ከጀመሩ 31 ቀናት ቢሆናቸውም ከትናንት ጀምሮ ግን ሙሉ በሙሉ አቋርጠው ከግቢው ወጥተዋል።

በየጊዜው አሳማኝ ያልሆኑ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲያነሱ የነበሩት ተማሪዎቹ ሰሞኑን ባልታወቀ ምክንያት ውሃ ውስጥ ገብተው ህይወታቸው ያለፈው የሶስት ተማሪዎች አማሟት ግልፅ አይደለም በሚል ሰበብ  ግቢውን እንደለቀቁ ገልጸዋል፡፡

"ከቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ውጤት በማምጣት ጉዳዩን በያዘው መርማሪ ፖሊስ፣በዩኒቨሪሲቲው አመራሮችና የተጎጂ ተማሪዎች ቤተሰብ ባሉበት አሟሟታቸው ከምንም ጋር የማይያያዝ መሆኑን ብንገልፅላቸውም ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ፍቃደኛ አልሆኑም "ብለዋል ።

ከተማሪዎቹ አሟሟት በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የገባልን ቃል አልፈፀመም የሚል ቅሬታ በማንሳት ጭምር ትምህርቱን ማቆማቸውን አመልክተዋል።

ተቋሙ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሲቀየር በወቅቱ የነበረው አመራር የላፕቶፕ ኮፒዩተሮች እንደሚሰጣቸው ፣ሁለተኛና ሶስተኛ  ዲግሪ የመማር እድል እንደሚፈጠርላቸውና  የሥራ እድል እንደሚመቻችላቸው  ቃል እንደተገባላቸውና ሳይፈፀምላቸው እንደቀረ ተማሪዎቹ በመከራከሪያነት እያነሱ መሆናቸውን ዶክተር ለሚ ተናግረዋል።

ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ዓመት ያሉ ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች በወቅቱ ቃል የተገባልን አሁኑኑ ካልተፈፀመ አንማርም በማለት ትምህርታቸውን ከአንድ ወር በላይ ማቆማቸውን ፕሬዘዳንቱ አስረድተዋል።

በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በነበረው የውጭ ዜጋ  ቃል የተገባው ላፕቶፕ ኮፕዩተሮችን ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው የሁለተኛና ሶስተኛ  ዲግሪ መስጠትም ሆነ የሥራ እድል መፍጠር በተቋሙ  አቅም  እንደማይቻል ነው የገለጹት።

ሆኖም  የተቋሙና የሀገሪቱ  አቅም በፈቀደ የትምህርት እድል እንደሚመቻችላቸውና የሥራ እድሉን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር እንደሚፈጥርላቸው  ብሎም ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ዲግሪ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን  ዶክተር ለሚ አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ ይህን እውነታ እንዲቀበሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ባሉበት ውይይት ቢደረግም መቀበል እንዳልፈለጉ ነው ያመለከቱት።

በዚህም ምክንያት ከአንድ ወር በላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ መስተጓገሉን ጠቅሰው ተማሪዎቹ የመጡለትን ዓላማ ወደ ጎን ትተው ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ እንዲያነሱ የሚገፋፋቸው  የፖለቲካ ነጋዴዎች አሻጥር መሆኑን ዶክተር ለሚ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ምግብ ና  የመኝታ አገልግሎት እያገኙ በፈለጉበት ጊዜ ስራ ማስተጓጎል  ስለማይቻል በተቋሙ የህግ የበላይነት እንዲከበር መንግስትና  ተቋሙ ተገቢው እርምጃ ለመውሰድ ከውሳኔ መደረሱን አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሮኒክስና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል የአምስተኛ ዓመት ተማሪና የወቅቱ የተማሪዎች ተወካይ ፍፁም ቱጁባ በበኩሉ  " በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት ከተቋረጠ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል" ብለዋል።

ህይወታቸው ያለፈው  ተማሪዎች የአስር ቀናት  ሀዘን በተማሪዎች ደረጃ ማወጃቸውንና ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል ያነሳነው ጥያቄ ሊመለስልን  ይግባል በማለት ትምህርቱ እንዳይቀጥል መደረጉን  ገልጿዋል።

በ2007 ዓ.ም. በወቅቱ ተቋሙ ሲመሩ በነበረው የውጭ ዜጋ በአፍ ደረጃ የላፒቶፕ ኮሚዩተሮችን ጨምሮ የሁለተኛና ሶስተኛ  ዲግሪ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባለቸው አመልክቷል።

ዩኒቨርስቲው በሚችለው አቅም ከተማሪዎች የተነሰውን ጥያቄ ለመመለስ ቃል የገባ ቢሆንም ተማሪዎቹ ይህን መቀበል ባለመቻላቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ መስጓጎሉን አስረድቷል።

የተማሪዎቹ ተወካይ በማያያዝም  ተማሪዎች ግዴታቸው የሆነውን የመማር ሂደቱን በማስቀጠል መብታቸውን ሊጠይቁ ይገባል እንጂ የመጡበትን  ዓላማ መዘንጋት ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም