የግሉ ዘርፍ በአገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ይገባል ተባለ

98

አዲስ አበባ ጥር 9/2011የግሉ ዘርፍ በአገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና የመሰረተ ልማት አቅርቦቱን ማሻሻል እንደሚገባ የግል ባለሀብቶችና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹት የግል ባለሀብቶችና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንደተናገሩት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና አገሪታ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ በባለ ድርሻ አካላት በኩል በርካታ የማሻሻያ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል።

በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አማረ በሻህ ለማምረቻው ዘርፍ ተገቢ ድጋፍ ያለመኖር፣ ፍትሃዊነት የጎደለው የግብር አከፋፈል ስርዓት፣ የመስሪያ ቦታ እጦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የፋይናንስና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በቅርብ ወራት የአገሪቷን የንግድ ስርዓት ለማሻሻል ጅምሮች መኖራቸው መልካም መሆኑን የገለጹት ባለሀብቱ፤ በዘርፉ ማነቆ የሆኑትን ችግሮች  ለመፍታትም ተገቢው ድጋፍና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በቱሪዝምና በአበባ ምርት ላኪነት የተሰማሩት ወይዘሮ ሳምራዊት ሞገስ በበኩላቸው በአንዳንድ የመንግስት አካላት በኩል ለግሉ ሴክተር  የተዛባ አመለካከት መኖሩን አንስተው ሴክተሩን እንደ ኢኮኖሚው ደጋፊ አድርጎ ማየት ይገባል ብለዋል።

በባለ ድርሻ አካላት በኩል አዲስ መመሪያዎችና ህጎች ስራ ላይ ከመዋላቸው በፊት የግል ሴክተሩን ማወያየት እንደሚያስፈልግ ገልጸው በውይይቶች ላይ የሚነሱ ሀሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ በኩልም ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።  

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር በላይ ፍሌ በበኩላቸው የግሉ ሴክተር የአገሪታ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል መሰራት ያለባቸው ስራዎች ላይ ጥልቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።

ዜጎች ስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ አመለካከት ላይ  መሰራት ይኖርበታል ብለዋል።

ይህም አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ብቻ ስራ የሚጠብቅ ሳይሆን ስራ ፈጠራ ላይ በስፋት እንዲሰማራ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር በላይ ገለጻ በአገሪቱ የምጣኔ ሀብታዊ መዋቅር ላይ በአብዛኛው ትልቅ ድርሻ ይዘው ያሉት ጥቃቅን፣ አነስተኛና መለስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች የአቅም ማነስ ችግሮችና ለስራ ምቹ ያልሆኑ በርካታ ማነቆዎች ያጋጥማቸዋል።

የፋይናንስ፣ የአስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችንም በጥልቀት በማየት መስራት ይገባል ብለዋል።

እነዚህ ጉዳዮች ላይ ከተሰራ የግሉ ሴክተር የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት እንዲሆንና በአገሪቱ በሚፈለገው መጠን የስራ እድል መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለፉት 15 ዓመታት በአማካይ በ10 በመቶ እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ።

ይህንን ዕድገት ማስቀጠል የሚቻለው የግል ዘርፉን ተወዳዳደሪ ለማድረግ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ምህዳር ሲፈጠር ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በተደጋጋሚ የሚነሳውና ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ያልሆነች አገር መሆኗን  ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህን የሚፈታና በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ነው ያሉት።

የዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለንግድ ዕንቅስቃሴ ባላት  የምቹነት ደረጃ ከ190 አገራት መካከል 159 ላይ ትገኛለች።

ይህም የአገሪቷን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና ዕምቅ አቅም የማያሳይ ከመሆኑ ባለፈ ከግል ዘርፉ የሚፈለገውን የስራ ዕድልና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማግኘት የሚያስችል አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ያለውንና በአገሪቱ ለግል ዘርፉ ዕድገት ምቹ ያልሆነ አሰራር ለመቀየር የሚያስችል አዲስ ኢንሼቲቭ(የሪፎርም ዕንቅስቃሴም) ተጀምሯል።

ከማሻሻያ ስራዎቹ መካከልም በዋነኛነት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት  የሚከናወኑ ስራዎች ሙሉ ለመሉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት በየሚንስትሩ ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው ከሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ እስከ 3 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ የአጭር፣ የመካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅዶች መቀመጣቸውንም አቶ አበበ አክለዋል።

አቶ አበበ እንደገለጹት የንግድ ምቹነት የማሻሻያ ስራዎችንና መሟላት የሚገባቸውን ስራዎች ከግል ዘርፉ ጋር በመመካከር በጋራ ይሰራሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም