በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚመክር የመሪዎች ስብሰባ በዝግ እየተካሄደ ነው

118

አዲስ አበባ  ጥር 9/2011 በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚመክር የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ በዝግ እየተካሄደ ነው።      

በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የርዋንዳው ፕሬዚዳንት ፓል ካጋሜ በተጠራው ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የህብረቱ አገራት መሪዎችና የልዑካን ቡድን አባላት ተገኝተዋል።

የመሪዎቹ ስብሰባ ዓላማ በቅርቡ በዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ  የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ለተከሰተው አለመረጋጋት ዕልባት ማምጣት ነው ተብሏል።

በአገሪቷ በተካሄደው ምርጫ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ ፍሊክስ ሺሴኪዲ እንዳሸነፉ ባለፈው ሳምንት ከታወጀ በኋላ አገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ርቋታል።

ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የፍሊክስ ዋነኛ ተፈካካሪ የነበሩት ማርቲን ፋዩሉ የምርጫ ውጤቱ ተጭበርብሯል፤ ውጤቱን አልቀበልም በማለታቸው ነው።   

በተፈጠረው አለመረጋጋት የሰው ይህወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል።    

ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በስብሰባው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ አባል አገራቱ በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ  የተከሰተው የሰላም እጦት መፍትሄ እንዲያገኝ የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው። 

''ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሟታል፤ ዘላቂ እልባት እንዲመጣ ያለንን አጋርነት ማሰየት አለብን'' ሲሉ ነው ፖል ካጋሜ የተናገሩት።

አገሪቷ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንድትመጣ ጥረት እያደረጉ ያሉ ተቋማትና ድርጅቶች ምስጋና እንደሚገባቸውም ፕሬዚዳንት ካጋሜ ገልፀዋል። 

''እኛ እዚህ የተገኘነው ለዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለንን አጋርነት ለማሳየት፤ የዚሁ ስብሰባ ዓላምም ይሄንን ማረጋገጥ ነው'' ያሉት ደግሞ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ናቸው።   

አክለውም በአገሪቷ የታየው ሕግን የጣሰ ተግባር መሆን ያልነበረበት ነው ያሉት ሊቀመንበሩ ሁሉም ወገኖች ኃይል ከመጠቀም መቆጠም አለባቸው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።  

ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት እንደሆነ ያስገነዘቡት ሊቀ መንበሩ የተፈጠረው ችግር ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መፍትሄ የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ በተፈጠረው ችግር ሳቢያ በውይይቱ ላይ አልተገኙም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም