ተቋራጮችና አማካሪዎች በመንገድ ስራ የሚሳተፉት በስራ አፈፃፀማቸው ነው - ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ

52

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 ከዚህ በኋላ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች በመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የሚሳተፉት በስራ አፈፃፀማቸው ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።

በከተማዋ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ገንዘብ፣ ጊዜና ጥራትን መሰረት በማድረግ መከናወን እንዲችል አዲስ አዋጅ እንዲወጣ ተደርጓል።

ምክትል ከንቲባው ለመንገድ ፕሮጀክት ስራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና የክፍለ ከተማ አመራሮች በቀጣይ የመንገድ ግንባታ አሰራር ዙሪያ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ "በብድርና በህዝብ ገንዘብ የሚገነቡት የመንገድ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ በርካታ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ ባክኖባቸዋል"።

"በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጠያቂም ተጠያቂም ባለመኖሩ በጥቂት ግለሰቦች ትዕዛዝ በጨረታ ሰበብ በተጭበረበረ መንገድ ህዝቡ የሚፈልገውን የመሰረተ-ልማት ግንባታ አላገኘም" ሲሉም ገልጸዋል።

ለአብነትም በሁለት ዓመት ሊጠናቀቁ ውል የተያዘላቸው ፕሮጀክቶች እስከ 10 ዓመት ሲጓተቱና ከተመደበላቸው በጀት እጥፍ ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም ከዚህ በኋላ የግንባታ ስራ ተቋራጮችም ሆነ አማካሪዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ የስራቸው አፈፃፀም ከጥራት ቴክኒክና ከጊዜ አንፃር እየተገመገመ እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

"አጭበርብረውም ሆነ በህጋዊ መንገድ የግንባታ ፈቃድ ስላላቸው ብቻ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመያዝ ቅድሚያ ክፍያ ከወሰዱ በኋላ ግንባታውን ለሚያቋርጡ፣ ለሚያጓትቱና ተጨማሪ ገንዘብ ለሚጠይቁ ስራ ተቋራጮች ቦታ የለንም" ብለዋል።

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት የስራ ተቋራጮችም ሆነ አማካሪዎች ፈቃድ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን በተሰጣቸው ፕሮጀክት ላይ ያላቸው ቁርጠኝነት፣ የኃላፊነት ስሜትና አፈፃፀም ታይቶ በሌሎችም እንዲሳተፉ ይደረጋል።

ከአሁን በፊት ያላቸውን አፈፃፀም በመገምገም ኮንትራታቸው የተቋረጠ እንዳሉ የገለጹት ኢንጂነር ታከለ፤ የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ ለግንባታ ኢንዱስትሪው ማደግ አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ቅድሚያ እንሰጣለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ሲከናወኑ የነበሩ ፕሮጀክቶች ጠያቂና ተጠያቂ በሌለበት የህዝብና መንግስትን ገንዘብ ያለ አግባብ ሲመዘብሩ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚወጣው ገንዘብ ባለሙያዎች እንደፈለጉ በሚተምኑት የሚከናወን ሳይሆን አመራሩ ፍሰቱን የሚቆጣጠርበት ስርዓትም ይኖራል ብለዋል።

"መንግስት ወለድ እየከፈለ በሚበደረው ከድሃ ህዝብ በሚወጣው ገንዘብ ላይ ልጓም እንደሌለው ፈረስ እንደፈለጉ መጋለብ ከዚህ በኋላ መቆም ይኖርበታል" ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገዶች ፕሮጀክት በምክትል ከንቲባው እንዲመራ ከተደረገ በኋላ፤ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።  

መንግስት፣ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች በከተማዋ ያለውን የተበላሸ አሰራር ለማስተካከል ከዛሬ ጀምሮ ቁርጠኛና ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም