ዩኒቨርሲቲው በ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያከናወነ ነው

114

ሰመራ ጥር 9/2011 የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ በሁለት ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ግንባታው ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር የሚጣጣምና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የዩኒቨርስቲው  ፕሬዚዳንት  ዶክተር አደም ቦሪ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የተማሪዎችና የመምህራን መኝታ ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣የመመገቢያ አዳራሾችና ቤተ መጻህፍት በግንባታው ተካተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተጀመረው የማስፋፊያ ግንባታ የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር ግቢ የመሠረተ ልማት ተቋማት ደረጃ የማሳደግና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ የዩኒቨርስቲውን የተማሪዎች የቅበላ አቅም አሁን ካለበት 7 ሺህ 500 ወደ  17 ሺህ ለማሳደግ እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡

የማስፋፊያ ግንባታው ዩኒቨርሲቲውን ለመማር ማስተማሩ ሥራ ምቹ ለማድረግ  መሆኑን ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፣ይህም ሞቃታማውን የአየር ጸባይ የሚቋቋምና ቀዝቃዛ የመጠጥ ውሃ በቧንቧ ለተማሪዎችና ለመምህራን የሚያቀርብ ቴክኖሎጂ እንደተካተተበት ገልጸዋል፡፡

ግንባታቸው እየተካሄዱ ያሉት 16 ህንፃዎች ያሏቸው መኝታ ክፍሎች 8 ሺህ 600 ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ሲሆኑ ፣ቤተ መጻህፍትና መዝናኛ ክፍሎች እንዳሏቸውም ተናግረዋል።

ለመምህራን መኖሪያነት የሚውሉ 144 የመኝታ ክፍሎች እየተገነቡ መሆኑን አመልክተው፣ እነዚህ ለጥናትና ለምርምር ሥራዎች ጭምር አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው በመሰራት ላይ እንደሚገኙ  ገልጸዋል፡፡

ዶክተር አደም እንዳሉት በአምስት ሕንፃዎች  ውስጥ የሚካተቱ የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተካሄደ ነው፤ ዘመናዊ ቤተ መጻህፍት ለመገንባት ጨረታውን ካሸነፈው ድርጅት ጋር ውል ተፈጽሟል።

ግንባታው አካል ጉዳተኞችን ግምት ውስጥ በማስገንባት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ በክሪ አህመድ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ  የመማር ማስተማር ሂደቱን በተመቻቸ ሁኔታ ለማካሄድና የመምህራንን ፍልሰት ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቀት በስምንት ኮሌጆች በ47 የትምህርት ክፍሎች የመማር ማስተማር ስራውን እያከናወነ የሚገኘው የሰመራ ዩኒቨርስቲ ከተመሰረተ10 ዓመታትን  አስቆጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም