የህብረት ስራ ማሀበራት 40 ቢሊዮን ብር እያንቀሳቀሱ ነው

85

አዳማ ጥር 9/2011 በሀገሪቱ የሚገኙ  የህብረት ስራ ማህበራት 40 ቢሊዮን ብር በማንቀሳቀስ ለምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

ኤጀንሲው በገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አማካይነት የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎትን በሀገር ደረጃ ለማስጀመር ያዘጋጀው የትግበራ ሰነድ ዛሬ በአዳማ ከተማ ለውይይት አቅርቧል።

በዚህ ወቅት የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ለጋዜጠኞች እንዳሉት በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የህብረት ስራ ማህበራት የአባላት ቁጥር 20 ሚሊዮን ደርሷል ።

"ከአባላቱ መካከል 32 በመቶ ሴቶች 15 በመቶ ደግሞ ወጣቶች ናቸው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ተደራሽነት እያደገ  መምጣቱን አስረድተዋል ።

ማህበራቱ  የካፒታልና የቁጠባ አቅማቸው 40 ቢሊዮን ብር እንዳደረሱ አመልክተው ይህንን በማንቀሳቀስ  ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

5 ሚሊዮን አባላት ያቀፉ የቁጠባና የብድር ህብረት ስራ ማህበራት 16 ቢሊዮን ብር በመቆጠብ  ገንዘቡ ተመልሶ ወደ ምጣኔው ሀብት በመግባት ግብርናን ለማዘመን ተግባር እየዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አቶ ኡስማን " ከተቆጠበው ገንዘብ በብድር ተጠቃሚ የሆኑ ማህበራት 870 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም በግብርና ምርት ላይ እሴት ጨምረው ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ "ብለዋል ።

ማህበራት ኑግ ፣ ሰሊጥና ሌሎች የቅባት ሰብሎችን ወደ ዘይትነት በመቀየር የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደጀመሩ አስረድተዋል ።

በሀገር ምጣኔ ሀብት ፣ በማህበራዊ ልማትና በሰላም ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሎ  በህብረት ስራ ማህበራት አማካይነት የወለድ አልባ የፋይናንሰ አገልግሎትን በሀገር ደረጃ ለማስጀመር የተዘጋጀው የትግበራ ሰነድም ዛሬ በአዳማ ከተማ ለውይይት ቀርቧል ።

ሀገራዊ የቁጠባ አቅም በማሳደግ  ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀው "ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልገሎቱ በዋናነት የእስልምና ኃይማኖት አስተምሮትን መነሻ ያደረገና ሸሪአዊ ድንጋጌዎችን ተከትሎ የሚሰራ ነው "ብለዋል ።

አገልግሎቱ ኃይማኖታዊና ሰብአዊ እሴቶችን በመገንባት የጋራ መረዳዳትንና መተሳሰብን የሚያጠነክር ነው ተብሏል ።

በትግበራ ሰነዱ ላይ ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ  የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች ፣ የኢትዮጵያ ዑለማዎች ፈቱሃና ደዕዋ ምክር ቤት አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል ።

የውይይቱ ዓላማ በትግበራ ሰነዱ ላይ ግልፅነት ለመፍጠር ፣ መካተትና መውጣት ያለባቸው ካሉ የግብአት ሃሳቦች ለማሰባሰብና አገልግሎቱን ለማደረስ  የተሳታፊዎችና ፈፃሚዎች ሚና በግልፅ ለማስቀመጥ መሆኑን በኤጀንሲው የብድርና ቁጠባ ከፍተኛ ባለሙያ  አቶ ታደሰ ጌታቸው ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም