በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የአድዋ ማስታወሻ የባዶ እግር ሩጫ ደራርቱ በአምባሳደርነት ትሳተፋለች

114

አዲስ አበባ ጥር 9/2011የአድዋ ድልን የሚዘክር የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ሊካሄድ ነው።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር  አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የውድድሩ አምባሳደር በመሆን በጎዳና ሩጫው ላይ እንደምትሳተፍ ገልጻለች።

የውድድሩ አዘጋጆች የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ሆራ ኢቨንተስ በጋራ በመሆን በሰጡት መግለጫ፤ ውድድሩ “ኑ ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ለአድዋ ድል በባዶ እግር እንሩጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።

የውድድሩ መነሻና መድረሻ መስቀል አደባባይ ሲሆን እስከ 35 ሺህ ሰው ይሳተፍበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነጻነት ታከለ እንዳሉት፤ የውድድሩ አላማ አርበኞች በአድዋ ድል ያስመዘገቡትን ድልና የከፈሉትን መስዋዕትነት መዘከርና ማስታወስ ነው።

የጎዳና ሩጫው እንዲዘጋጅ ለአንድ ዓመት የተለያዩ ዝግጅቶች የተካሄዱ ሲሆን ቆይቶ ዘንድሮ ከሚከበረው 123ኛው የአድዋ ድል በዓል በተከበረ በማግስቱ ውድድሩ ይካሄዳል።

የአድዋን ድል የሚዘክረው የጎዳና ላይ ሩጫ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሄዶ የሚቆም ሳይሆን በየዓመቱ በቋሚነት የሚካሄድ ውድድር መሆኑን አስታውቀዋል።

"በአድዋ ድል ከተሳተፈው ሰራዊት 98 በመቶ የሚሆነው በባዶ እግር ተዋግቶ ድል እንዳደረገ ታሪክ ያስረዳል" በማለት የሆራ ኢቨንተስ ስራ አስኪያጅ ብስራት መንግስቱ ተናግረዋል።

ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ተሳታፊዎች የአርበኞቹን ህመምና ስሜት በተወሰነ መልኩ እንዲጋሩ የመጨረሻውን 500 ሜትር በባዶ እግር እንዲሮጡ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

እ.አ.አ በ1960 በሮም ኦሎምፒክ ሻምበልለ አበበ ቢቂላ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው በባዶ እግሩ ሮጦ እንደሆነ ያስታወሱት ስራ አስኪያጁ ጣልያን የሮም ኦሎምፒክን ስትዘክር በባዶ እግር የሚካሄድ የማራቶን ውድድር እንደምታካሂድ ገልጸዋል።

''እኛም ይሄን አኩሪ ታሪካችንን በስፖርቱ መስክ መዘከር እንደሚገባና በባዶ እግር መሮጥ ሀሳብም ከዚሁ የመነጨ ነው'' ብለዋል።

በሌላ በኩል የውድድሩ የክብር አምባሳደር የሆነችው አትሌት ኮሎኔል  ደራርቱ ቱሉ በጎዳና ሩጫው ላይ እንደምትሳተፍ ገልጻለች።

''ለመጨረሻ ጊዜ በውድድር የተሳተፍኩት ከስምንት ዓመት በፊት ነው ለሁለት ዓመት በፊት በህዳሴው ግድብ ሩጫ ተሳትፎ ነበረኝ ለአድዋው ሩጫ ልምምድ ሰርቼ 9 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩን በጫማ የተቀረውን 500 ሜትር በባዶ እግሬ ለመሮጥ ቃል እገባለሁ'' ብላለች።

የውድድሩ አምባሳደር ሆና በመመረጧ ከፍተኛ ኩራትና ክብር እንዲሁም እድለኝነት እንደሚሰማትና በአድዋ ድል እናቶችና አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው ያቆዩትን ታሪክና ጀግንነት ሁሉም በተሰማራበት መስክ ውጤታማ በመሆን በስራው ጀግና መሆን እንዳለበት ተናግራለች።

የሩጫው ምዝገባ ከሰኞ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጃን ሜዳ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት እንደሚጀምርና በቀጣይ በባንኮችም ምዝገባው እንዲካሄድ ያለው ዝግጅት ተጠናቆ ባንኮቹ ይፋ እንደሚደረጉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም