ምክር ቤቱ የ88 ነጥብ 33 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ

48

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ መንግስትና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረሰውን የ88 ነጥብ 33 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

የምክር ቤቱ የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብድር ስምምነቱን አስመልክቶ የውሳኔ ሃሳብና ማብራሪያ አቅርቧል።

በዚህ ጊዜ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሃድጎ እንደገለጹት፤ የብድር ስምምነቱ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ የታቀዱ ግቦች ለማሳካት ያለመ ነው።

በተለይም የብድር ስምምነቱ የስደተኞችን ችግር ለመቅረፍና የተወሰኑ የስራ እድሎችን የሚያመቻች ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ስደተኞችን አስመልክቶ የፈረመችውን አለምአቀፍ ስምምነት ለመተግበር የሚያግዝ ነው ሲሉ አክለዋል።

የብድር ስምምነቱ ከወለድ ነፃ፣ የስድስት ዓመት የእፎይታ ጊዜና በ38 ዓመት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑን ወይዘሮ ለምለም ጠቅሰው ይህም የወጪ ጫናው ያልበዛና ከአገሪቱ የብድር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ምክር ቤቱም የብድር ስምምነቱን ማብራሪያ ካደመጠ በኋላ በሶስት ተቃውሞ፣ በሶስት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም