ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ያጠናክራሉ

102

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥን ያካተተ የልዑካን ቡድን ትናንት በሳዑዲ አረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ በመገኘት ከሳዑዲው የገንዘብ ሚኒስትር ሞሃመድ አል-ጀደን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን አጠናከረው ለማስቀጠል መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የልዑካን ቡድኑ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚው ዘርፍ  በግብርና፣ በመሰረተ-ልማት፣ በኃይል ልማት፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሁም በንግድ ያላቸውን የቆየና የካበተ የኢኮኖሚ ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታችው ተገልጿል።

ትብብሩን በማስፋት የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ኢንቨስትመንት አጠናክረው እንዲቀጥሉና የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በነበራቸው ቆይታ ከሳዑዲ አረቢያ ገንዘብ ሚኒስትር በተጨማሪ ከግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ውሃ ሚኒስትር አብዱልረህማን ቢን አል-ፋድሊ ጋርም ውይይት አድርገዋል።

እንዲሁም ከሳዑዲ አረቢያ ልማት ፈንድ አመራሮች እና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በዝርዝር የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩም በመግለጫው ተገልጿል።

ሳዑዲ አረቢያ ሶስተኛዋ የኢትዮጵያ የንግድ ሸሪክ ስትሆን፣ ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የመሰረቱት በ1941 ዓ.ም እንደሆነ ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም