ሰቆጣ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የንግድ ትርኢትና በዛር ተከፈተ

54

ሰቆጣ ጥር 9/2011 በሰቆጣ ከተማ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ 43 የኢንተርፕራዝ አንቀሳቃሾች የተሳተፉበት የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ፡፡

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አየለ በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ወቅት እንዳሉት ዝግጅቱ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ እንዲያስተዋውቁ  ያግዛል፡፡

የኢንተርፕራዝ አንቀሳቃሾችን እርስ በእርስ ከማቀራረብ ባለፈ ከሸማቹ ህብረተሰብ ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

ከሰቆጣ ማረሚያ ቤት የመጣው  የኤግዚብሽኑ ተሳታፊ ወጣት ሀብቱ ቢምረው ንግድ ትርኢትና  ባዛሩ ላይ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ይዞ መቅረቡን ተናግሯል።

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚያመርቱት የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ለመሸጥ የገበያ ትስስር አለመኖሩን የጠቆመው ወጣቱ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ  የተዘጋጀው የንግድ ትርኢትና  ባዛር  ምርታቸውን ከመሸጥ ባለፈ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥርላቸው አስረድቷል፡፡

ጥልፎችን፣የመጋረጃ እና የአልጋ ልብሶችን በዝግጅቱ ያቀረቡት ወይዘሮ ካባ ይመር በበኩላቸው መንግስት ባመቻቸላቸው መስሪያና መሸጫ ሱቅ ምርታቸውን እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ካሁን ቀደም በተካሄዱ ተመሳሳይ ዝግጅቶች መሳተፋቸው ምርታቸውን ከመሸጥ ጀምሮ በማስተዋወቅ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻሉም አመልክተዋል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር በንግድ ትርኢትና  በዛሩ  ሲገበያዩ ያገኛቸው ወይዘሮ ሙሉ አረጋ በሰጡት አስተያየት በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ ምርቶችን በአንድ ቦታ በማግኘታቸው ይገጥማቸው የነበረውን የትራንሰፖርት ወጪ እና እንግልት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል፡፡

ከጥር 8/2011ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርኢትና  ባዛር  በኢንተርፕራይዞች የተዘጋጁ  ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት፣ የቤት ዕቃዎች፣ ጫማዎች፣ መጋረጃዎችና ሌሎችንም  ምርቶች ቀርበዋል፡፡

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ የሰቆጣ ከተማ ነጋዴዎች፣ ሸማቾችና የአመራር አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም