ውሃን ማዕከል ያደረገው ልማት ሕይወታችንን ቀይሮታል....በአፋር አርብቶ አደሮች

54

ሰመራ ጥር 9/2011 በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ በመንደር የተሰባሰቡ አርብቶ አደሮች ውሃን ማዕከል ባደረገው የልማት መርሀ ግብር ሕይወታቸው ወደ አርሶ አደርነት መቀየሩን ገለጹ።

የክልሉ እንስሳት፣ ተፈጥሮና ግብርና ልማት ቢሮ በበኩሉ 7 ሺህ አርብቶ አደሮች በተያዘው ዓመት በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ራሳቸውን በምግብ እንዲችሉና ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በዱብቲ ወረዳ አራዶናነኪስ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አብዱልቃድር አይደሩስ መሐመድ በወረዳው በመንደር ተሰባስበው መኖር ከጀመሩ ወዲህ በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ባገኙት ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሄክታር ከ60 እስከ 80 ኩንታል በቆሎ በማምረት ቤተሰባቸውን መመገብ ከመቻላቸው በላይ በዓመት እስከ 80 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

"በቆሎው በአገዳው ወቅት ለእንስሳት መኖ በመሆን ተጨማሪ ጥቅም እያገኘንበት ነው" ያሉት አቶ አብዱልቃድር፣ በቀጣይ ወደ አርብቶ አደርነት ሕይወት መመለስ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

ሌላው የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱልቃድር አይደሩስ ሐሞሎ በበኩላቸው ከአርብቶ አደርነት ሕይወት ከወጡ አራት ዓመታት እንደሆናቸው ነው የገለጹት።

"ውሃን ማዕከል ባደረገው የልማት መርሀ ግብር በእርሻ ሥራ ከተሰማራሁ በኋላ የእንስሳትን ጭራ ተከትሎ ከመሄድ ነጻ ወጥቻለሁ" በማለትም  ኑሯቸው በአዲስ የሕይወት መስመር መለወጡን ተናግረዋል።

በእርሻ ሥራው በዓመት እስከ 160 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆኑንም ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት አቶ አብዱልቃድር የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብአት መጠቀማቸውና የባለሙያዎች ድጋፍ ውጤታማ የእርሻ ሥራ እንዲያከናውኑ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በእርሻ ሥራ ከተሰማሩ ወዲህ የገበያ ዋጋ መዋዠቅ ዋነኛ ችግር ቢሆንባቸውም "በአርብቶ አደርነት ወዳሳለፍኩት ሕይወት ዳግም መመለስ አልፈልግም" ብለዋል።

የዱብቲ ወረዳ የእንስሳት፣ ተፈጥሮና ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከቢር ዩሱፍ በበኩላቸው  በወረዳው በመንደር የተሰባሰቡ አርብቶ አደሮች በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ሕይወታቸውን በመቀየር ላይ ይገኛሉ።

በወረዳው በሰብልና በጓሮ አትክልት ልማት የተሰማሩ ከ2 ሺህ 500 የሚበልጡ አርብቶ አደሮች በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት በነፍስ ወከፍ እስከ 100 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በመንደር የተሰባሰቡ 7 ሺህ አርብቶ አደሮችን ውሃን ማዕከል አድርጎ በተዘረጋው የልማት መርሃ ግብር ዘንድሮ ወደ እርሻ ልማት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ የገለጹት ደግሞ የክልሉ እንስሳት፣ ተፈጥሮና ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓሊ ሁሴን ናቸው።

እንደ ኃላፊው ገለጻ አርብቶ አደሮች በልማቱ ሕይወታቸውን ወደ አርሶ አደርነት በመለወጥ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ሕይወት መምራት ጀምረዋል።

በክልሉከ2004 ጀምሮ የተካሄደው የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር የሚፈለገውን ያህል ውጤት ባይገኝበትም የተወሰኑ አርብቶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በአዲስ መልክ መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

አቶ አሊ እንዳሉት ልማቱ በደጋማው የአገሪቱ አካባቢዎች ዘንቦ ወደ ክልሉ የሚገባውን ውሃ፣ የአዋሽ ወንዝ እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም የሚከናወን ነው።

ክልሉ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እንዳለው ጠቁመው፣ በመርሀ ግብሩ እያንዳንዳቸው በሰከንድ ከ30 እስከ 100 ሊትር የሚያመነጩ ከ30 በላይ የውሃ ጉድጓዶች ተጠናቀው ለአርብቶ አደሩ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።

አርብቶ አደሮቹ በሚያለሙት መሬት በምግብ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገቢ እያገኙ መሆኑንም አቶ ዓሊ አመልክተዋል።

የክልሉን አርብቶ አደሮች የድርቅ ተጋላጭነት ችግር ለማቃለልም በዱብቲ ወረዳ በ18 ሚሊዮን ብር በጀት የመኖ ባንክ መቋቋሙን ኃላፊው ተናግረዋል።

"በወረዳው በ700 ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ ባለው ልማትም እስካሁን ድረስ 900 ሺህ እስር መኖ ተዘጋጅቷል፤ ምርቱን ሁለት ሚሊዮን ለማድረስም በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ቢሮው በአምስት ወረዳዎች ለሚቋቋሙ ተመሳሳይ ባንኮች የቴክኒክ፣ የገንዘብና የምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 10 ሚሊዮን እንስሳትና ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይኖራል ተብሎ ይገመታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም