በአካባቢያው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን በሐረር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

1137

ሀረር ጥር 8/2011 በአካባቢያው የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት  እንዲስተካከል  በተደጋጋሚ  ቢጠይቁም ምላሽ አጥተው መቸገራቸውን በሐረር ከተማ  ነዋሪዎች ተናገሩ።

በከተማው በተለምዶ ሐኪም ጋራና ቢራ ፋብሪካ ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረቱ ሳይስተካከል የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ችግሩ ተደራራቢ ሆኖባቸዋል።

አቶ ደግሰው አሰፋ  የቢራ ሰፈር ነዋሪ ሲሆኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው ሁለት ሳምንት እንዳለፈው በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡

ችግሩ እንዲፈታላቸው ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቢጠይቁም  ጠብቁ  ከማለት ባለፈ መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

” በአካባቢው  የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ምክንያቱን በማይታወቅ ሁኔታ በተደጋጋሚ  ይቃጠላል፤  በዚህም አገልግሎት በማጣት ለችግር እንዳረጋለን”  ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ መሰረት ዳባ ናቸው፡፡

ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ አሰራር ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሀኪም ጋራ ሰፈር ነዋሪ አቶ አጀባ ጫላ በበኩላቸው ” የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ መቋረጥ ተማሪ ልጆቻቸውን በፈተና ወቅት ከጥናት እንዲርቁ ሆነዋል” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ችግሩ እንደፈተላቸው ቢጠይቁም በሰራተኞች በኩል አጥጋቢ ምላሽ በማጣት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የደንበኞች አገልግሎት ሽያጭና  ቅሬታ ሰሚ ክፍል ኃላፊ አቶ ካሊድ ጠሀ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በአካባቢው የኤሌትሪክ አገልግሎት የተቋረጠው ትራንስፎርመር በመቃጠሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ምክንያቱ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ በሚያጋጥመው የአቅም ማነስ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

 የተቃጠለውን ትራንስፎርመር ለመተካት  በክልሉና በአጎራበች ቀጠና ባለመገኘቱ ችግሩን በአጭር ጊዜ መፍታት እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ባለው ዋና መስሪያቤት  በሶስት ቀናት ውስጥ ችግሩ እንደሚፈታ አስታውቀዋል።

በአካባቢው ለተፈጠረው የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት መንስኤው በአርሶ አደር የካሳ ጥያቄ ጋር ተያይዞ  የኤረር ውሃ ፕሮጀክት እስካሁን ድረስ ባለመጠናቀቁ መሆኑን  የክልሉ  ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው።

ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋርም ትናንት በችግሩ ዙሪያ መወያየታቸውንና  አቅም በፈቀደ መልኩ የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።