በህክምና ተቋማት የሚውልዱ እናቶች ቁጥር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

73

አዲስ አበባ  ጥር 8/2011 በኢትዮጵያ በህክምና ተቋማት የሚውልዱ እናቶች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ተናገሩ።

የጤናማ እናትነት ወር ''በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ተከብሯል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደገለጹት በኢትዮጵያ 72 በመቶ የሚሆኑ እናቶች የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ በቤት ውስጥ ይወልዳሉ። 

በሌላ በኩል በአገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የጤና ተቋማትን ማስፋፋትና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ በኩል ስኬታማ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም እናቶች በህክምና ተቋማት ሄደው የመወለድ ልምድ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

እናቶች ከጤና ተቋማት ውጭ በሚወልዱበት ወቅት ከመጠን በላይ ደም መፍሰስ ስለሚያጋጥማቸው ለህልፈተ ህይወት የመዳረጋቸው አጋጣሚ እንደሚፈጠርም አስረድተዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴሩ በቤተሰብ ጤና ቡድንና በጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች አማካኝነት ለነፍሰጡር እናቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

እናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ባህል እንዲያዳብሩ ኀብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘላቂ የልማት ግብ የተቀመጠውን ከ100 ሺህ እናቶች 421 በወሊድ ወቅት ለህልፈተ ህይወት መዳረግ በአውሮጳውያኑ 2020 ቁጥሩን በግማሽ ለመቀነስ እንዲቻል የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም ዶክተር አሚር ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው በመዲናዋ ለእናቶች ህልፈተ ህይወት 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው በወሊድ ወቅት በሚያጋጥም የደም መፍሰስና ተያያዥ ችግሮች መሆኑን ገልጸዋል።

በወሊድ ወቅት የሚያጋጥመውን የደም መፍሰስ ችግር ለመፍታት ለቢሮው ተጠሪ የሆኑ 12 ሆስፒታሎችና 97 ጤና ጣቢያዎች ተንከባካቢ፣ ሩህሩህና ተገልጋይን አክባሪ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን የደም መፍሰስ ችግር ለመታደግ ኀብረተሰቡ ደም ልገሳን ባህል እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ከሁለት ቀናት በፊት የወለደችው ወይዘሮ ዘምዘም አህመድ በህክምና ተቋም በመገላገሏ ከደም መፍሰስ አደጋ እንደታደጋት ተናግራለች።

እናቶች በህክምና ተቋማት ቢወልዱ ለራሳቸውም ይሁን ለሚወለደው ህፃን ጤንነት ወጣኝ መሆኑንም መክረዋል።

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በተከበረው ''የጤናማ እናትነት ወር'' በዓል ላይ የጤና ሚኒስሩ ዶክተር አሚር አማን፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላና የበዓሉ ተሳተፊዎች ደም ለግሰዋል።

በእለቱ ከዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል እስከ ግዮን ሆቴል ድረስ የእግር ጉዞም ተደርጓል። 

የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13 ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም