ቤተ-እምነቶች ሰላምን ለማምጣት የሚጠበቅባቸውን አላበረከቱም

174

ጥር 8/2011 የሀይማኖት አባቶች ለሀገር እና ለህዝብ ሰላም መረጋገጥ በሚጠበቅባቸው ደረጃ ሳይሰሩ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን የእምነታቸውን ተከታዮች ለማስተማር እንደሚተጉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀይማኖት አባቶች ገልተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን በወንጌል መምሪያ የሚያገለግሉ ቄስ ጸጋነሽ አየለ እንዳሉት “ሰላምና ሀይማኖት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው ለሰላም መስራት ግድ ነው” ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የሰላም እጦት ችግርን ለመቀነስ ያልተቻለው አንዳንድ መምህራን የግል ጉዳያቸውን በማስቀደም  የሀይማኖት አስተምህሮን  ወደ ጎን በመተው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

“እንደ ሀይማኖት መሪነቴ የኔ ማንነት ክርስትና ከሆነ፤ የክርስትና ተቃራኒ ከኔ መውጣት የለበትም” ያሉት ቄስ ጸጋነሽ “መሳደብ፣መጥላት፣መናቅ፣ማቅለልም፣የበላይነት መታየት የለበትም ከዚም አልፎ ይቅርታ ካላደረኩ፤ በቀልንም ካሰብኩ ሀይማኖተኛ አይደለሁም ማለት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው ያሉት የህይማኖት መሪዎችም በግላቸው፣ በቤተሰባቸው፣ በአከባቢያቸው ብሎም በሀገር ደረጃ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ተከትለው ባለስራታቸው በተለያዩ በሀገሪቱ ክፍሎች የሰላም ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል በማለትም አስረድተዋል፡፡

የእምነት መሪዎች የሀይማኖትን እሴት ከፖለትካና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ሳይቀላቅሉ በማስተማር ሰላምና እድገትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የተናገሩት ቄስ ጸጋነሽ ለዚህም ከምንጊዜውም  የበለጠ ተግተው እንደምሰሩ  አስረድተዋል፡፡

“እኛ የሀይማኖት መሪዎች ተከታዮቻችንን በሚገባ ባለማስተማራችን፣ ሀይማኖታዊ ስነምግባርና የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን አርያ ባለመሆናችን በተለይም ሀገር ተረካቢ ትውልድ በአግባቡ አልቀረጽንም” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ አባ ላእከማሪያም ገብረ ስላሴ ናቸው ፡፡

አባ ላእከማሪያም እንዳሉት “እኛ አባቶች በእምነት አስተምህሮ ህብረተሰቡን ስለሰላም  የማስተማር ተግባርን በማጠናከር  ለሀገሪቱ ሰላም ያለንን ድርሻ በአግባቡ መወጣት ይገባናል’’ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነየሱስ  ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቄስ ጥላዬ ከበደ በሰጡት አስተያየት እንደ ሀይማኖት መሪነታቸው  ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን በማስገንዘብ በኩል የሰሩት ስራ ዝቅተኛ በመሆኑ አሁን ለተፈጠረው ስጋት መፍትሄ ማምጣት  እንዳይቻል አድርጓል ብለዋል፡፡

ከነዚህ ችግሮች ለመውጣትም መሪዎችም ሆኑ ተከታዮች ሀገርን ለማዳን ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አስረድተዋል።  

የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማምና የአዲስ አበባ ኢማሞች ዋና ጸሓፊ ሃጅ ጠሃ ሃሩን በበኩላቸው “በሀገራችን አንዳንድ አከባቢዎች በሰላም እጦች ምክንያት በዜጎች ላይ እየደረሰ ካለው ችግር ብቻ መማር በቂ ነው፤ ይህ ችግር እኔ ላይ  ቢደርስ ብሎ ማሰብ ግድ ነው፤ ከዚህ ነው የሰላም ዋጋን ማወቅ የሚቻለው” በማለት አብራርተዋል፡፡

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከንብረታቸውና ከቄያቸው ተፈናቅለው ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጡ ያደረገውም  የሰላም እጦት እንደሆነ ተናገረዋል፡፡

ሁሉም ሰው የሌላውን ሰላም ሲጠብቅ የራሱ ሰላም  እንደሚጠበቅ በመረዳት ለሰላም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ያሉት ሃጂ ጦሃ “የተሻለ ሀገር የነበረችው ሶሪያ ዛሬ ላይ በሰላም እጦት ምክንያት ዜጎቿ  ወደ ሀገራችን መጥተው በየመስጂዱ እየለመኑ ማየት ከዚህ በላይ ልብ የሚናካና የሚያስተምር የለም” ብለዋል፡፡

“በአንድ አከባቢ ሰላም መጥፋት የሚያደርሰው ጉዳት በዜና ሰምተን መሸማቀቁ ራሱ ከመጥፎ ተግባር ሊከለክለን ይገባል” ሲሉም ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገሪቱ ለውጦች እየታዩ እንደሆነና ለለውጡ ሰፊ ድርሻ  ሊኖራቸው እንደሚገባ  የተናገሩት ሃጂ ጦሃ፤  ኡለማዎች እንደ ሀይማኖት መሪዎች አርያ ሆነው መገኘት እንደሚያስፈልግ  ምክር እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ወጣቱ “የሰላም መጥፋትና መኖር ውስጥ እኔም ድርሻ አለኝ” ብሎ ግንዛቤ እንዲያገኝ በየደረጃው ያሉ የእስልምና ሀይማኖት መምህራን እንዲያስተምሩ ለማድረግ በቀጣይም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም