በካማሽ ዞን የተቋረጠውን የጤና ተቋማት አገልግሎት ለማስጀመር እየተሠራ ነው

71

አሶሳ ጥር 8/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በጸጥታ ችግር የተዘጉ የጤና ተቋማትን እንደገና ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የመጀመሪያው ዙር የሕክምና ቡድን የተዘጉ ጤና ተቋማትን ለማስጀመርና ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ወደዞኑ መንቀሳቀሱም ተመልክቷል። 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በካማሽ ዞን ተፈጥሮ በነበረ የጸጥታ ችግር በዞኑ አምስት ወረዳዎች የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ማቋረጣቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ፍሬሕይወት እንዳሉት በሽታን አስቀድሞ ለመከላል ተግባራዊ የሆነው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምም በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መቋረጡን አመልክተዋል።

እንደኃላፊዋ ገለጻ በዞኑ ባለፉት ሦስት ወራት ሦስት ነፍሰጡር እናቶችና አምስት ህጻናት በወሊድና በሕክምና አገልግሎት እጦት ሕይወታቸውን አልፏል።

 “የዞኑ የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ የጤና ተቋማቱን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደገና ለማስጀመር ቢሮው ተግባራዊ ዕቅድ አዘጋጅቷል” ብለዋል፡፡

በዕቅዱ መሠረት ለመጀመሪያው ዙር የሕክምና ቡድን ስልጠና ተሰጥቶ ወደአካባቢው ከትናንት በስቲያ እንዲንቀሳቀስ መደረጉን አስረድተዋል።

የሕክምና ቡድኑ በመንገድ እጦት ምክንያት ፈጥኖ መንቀሳቀስ ባይችልም ቡድኑ ሰሞኑን በዳቡስ ወንዝ በኩል በታንኳ ተሻግሮ ወደ ዞኑ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት የበጎ ፈቃደኛ ህክምና ቡድን በአምስት ተከታታይ ዙሮች የሚንቀሳቀስ ሲሆን ዋነኛ ተግባሩም የተዘጉ ተቋማትን በመክፈት እንደገና ሥራ ማስጀመር ነው፡፡

በግጭቱ ወቅት አካባቢውን ለቀው የወጡ የጤና ባለሙያዎችን ለመመለስ ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑንም ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡

ዞኑ ሞቃታማ በመሆኑ ወባን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ቢከሰቱ አስቸኳይ ሕክምና ለመስጠት እንዲቻል ገንዘብ፣ መድኃኒትና የሕክምና መሳሪያ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከረጂ ድርጅቶች የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የዕቅዱ ተፈጻሚነት በየሳምንቱ ክትትል እንደሚደረግበት የገለጹት ኃላፊዋ፣ በግጭቱ ምክንያት አካባቢውን ለቀው የወጡ የጤና ባለሙያዎች ተመልሰው ሥራቸውን እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር ወደዞኑ የተንቀሳቀሰው የበጎ ፈቃደኞች የሕክምና ቡድን አስተባባሪና በአሶሳ ሆስፒታል ጠቅላላ ኃኪም የሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አበራ ቡድኑ በተሟላ ባለሙያና የህክምና ቁሳቁስ መደረጀቱን ተናግረዋል፡፡

“የዞኑ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስ ለህብረተሰቡ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል” ብለዋል፡፡

የካማሽ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገርቢ ሎላሳ በበኩላቸው መስተዳድሩ ለበጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ተሸከርካሪ ከመመደብ ጀምሮ ወጪአቸውን በመሸፈን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በሎጅጋንፎይ፣ ያሶ፣ ሰዳል፣ አጋሎሜጢ እና ካማሽ በተባሉ ወረዳዎች የተዋቀረው የካማሽ ዞን ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖርበት ይገመታል፡፡

በዞኑ በየወረዳው አንድ ጤና ጤቢያ እና በርካታ ጤና ኬላዎች አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ከቢሮው የተገኘው መረጃ ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም