ከካፋ ዞን የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው

68

ሀዋሳ ጥር 8/2011 ከካፋ ዞን ወደ ከምባታ ጠምባሮ ዞን  ተፈናቅለው የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበራ ዊላ ለኢዜአ እንዳሉት  በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ከአስር ዓመታት በላይ የቆየ የሰፈራ ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡

በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የከምባታ ጠምባሮ ነዋሪዎች በአካባቢው ንብረት አፍርተው የቆዩ ቢሆንም ካለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ ምክንያቶች ከነበሩበት ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ባሉ ሶስት የአርብቶ አደር አካባቢዎች ወቅትን ጠብቆ በሚከናወን የከብት ዝርፊያ ሳቢያ የሚከሰቱ ግጭቶች ቢኖሩም የአሁኑ ከሃገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ የተደራጁ ኃይሎች የተሳተፉበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አቶ አበራ እንደገለጹት ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ 20ሺ 156 የሚሆኑ የከምባታ ጠምባሮ አካባቢ ተወላጆች  ከካፋ ዞን ወደ ቀደሞ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡

በቅርቡ ያጋጠመውን ችግር ተከትሎም የተፈናቃዮቹ ቁጥር እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡

የፌደራልና የክልሉ መንግስትም ለሶስት ዙር የተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ሰብአዊ ድጋፎችን ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ቀድሞ ወደመጡበት ወረዳና ቀበሌ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር እንዳሉ ድጋፉን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም  አመልክተዋል፡፡

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ሃብት ንብረት ወዳፈሩበት ወደ ካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ለመመለስ ኮሚሽኑ የባለሙያና አመራር ቡድን ከሳምንት በፊት ወደ አካባቢው መላኩን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

"ቡድኑ በዋናነት የአካባቢውን ሰላም የማስጠበቅና በመሰረተ ልማት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከካፋ ዞን አስተዳደር ጋር እየተወያየ ነው" ብለዋል፡፡

በሰፈራ ጣቢያው አካባቢ ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የኮሚሽኑ ጨምሮ የውሃና መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም አመራሮች ትናንት ወደ ስፍራው ማቅናታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አካባቢውን ከግጭት ቀጠና ነጻ በማድረግና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ተፈናቃዮችን ለመመለስ  የሚከናወነው ስራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የከምባታ ጠምባሮ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ታከለ ነጫ በበኩላቸው በአካባቢው በተፈጠረው ችር ዙሪያ ከካፋ ዞን አስተዳደር ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ከተመዘገቡ ተፈናቃዮች በተጨማሪም በወረዳው በተለያየ መንገድ እየገቡ ያሉ በመኖራቸው ሰብዓዊ ድጋፉ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

ጥቃቱ በታጠቁ ሽፍታዎች እንደተፈጸመና የሰው ህይወት እንዳለፈ የተናገሩት ደግሞ የካፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው፡፡

ወደ መጡበት አካባቢ ከተመለሱት በተጨማሪ የካፊቾና ቤንች ተፈናቃዮች በሦስት ቦታዎች ተጠልለው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር እየተሰራ እንደሆነና በአካባቢውም  ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም