አምራች ኢንዱስትሪዎችና ጦሳቸው

68

ሙክታር ሁሴን (አዳማ ኢዜአ)

አገራችንን  ጠፍንጎ ከያዛት ድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅና የዜጎቿን የአኗኗር ዘይቤ በማሻሻልመካክለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ከኋላ ቀር የግብርና አሰራር መላቀቅ የግድ ይላል።

ይህንኑ ለማሳካት የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊስና ስትራቴጅ በመቅረፅ ህጎችና ደንቦችን በማዘጋጀት በሀገሪቷ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ወደ ተግባር ከተገባ ሰነባብቷል።

መንግስት የዜጎችን ህይወት ለመለወጥና ለማሻሻል የሚያስችሉ ከአካባቢ አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ፣በህብረተሰቡ ጤንነትና የአኗኗር ዜይቤ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በማያስከትል መልኩ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጅ ትግበራ ከተጀመረ ከ15 ዓመታት በላይ ሆኖቷል።

በዋናነት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሰረት ባደረገ መልኩ ፣ አነስተኛ መካክለኛና ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት በማስፋፋት በሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና ከማበርከታቸውም ባለፈ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል።

የኢንዱትስሪ ልማት ፖሊስና ስትራቴጂ አተገባበር የታለመለትን ግብ እያሳካ ቢሆንም ከኢንቨስትመንት መሬት አዘገጃጀትና አሰጣጠጥ ጀምሮ የአምራች ኢንዱስትሪዎች በርካታ ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን በአካባቢ ደንና አየር ንብርት ለውጥ ኮሚሽን የህግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ መህሪ ወንድማገኝ ይናገራሉ።

ማንኛውም ኢንቨስትመንት የሚከናወነው ለዘርፉ ልማት አመቺ የሆነ መሬት አዘገጃጀት፣በአካባቢ አየር፣በህብረተሰቡ ጤንነትና የአኗኗር ዜይቤ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በማያስከትል መልኩ እንዲተገበር ፖሊስዎችና የህግ ማእቀፎች መደንጋገቸውን ይገልፃሉ ።

የሀገራችን አምራች ኢንዱስትሪዎች ከተሰጣቸው መሬት ጀምሮ በአካባቢ ፣በህብረተሰቡ ጤንነትና የአኗኗር ዜይቤ ላይ እያስከተሉ ያሉት መዘዝ  ህዝቡ ቅሬታ እንዲያሳድር በር መክፈታቸውን ዳይሬክተሩ አጫውተውኛል።

ከአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚወጣው የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣የኬሚካል አጠቃቀምና አወጋገድ ላይ ሰፊ ክፍተት ይታይበታል ።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞንና ምስራቅ ሸዋ በተለይም አዳአ፣ ሉሜ፣  አዳማ፣ ሱሉልታ፣ሰበታ ሐዋስና ቡራዩ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ማእከል መሆናቸው ይታወቃል ።

አቶ ማህሪ እንዳሉት የተጠቀሱት አካባቢዎች ለመዲናችን አዲስ አበባ ካላቸው ቅርበትና የሀገሪቷ መውጫና መግቢያ በሮች መዳረሻ በመሆናቸው ለማንኛውም አይነት ኢንቨስትመንት ካላቸው ተመራጭነትና አዋጭነት አንፃር የባለሃብቶች ቀልብ በመሳብ ቀዳሚዎቸ ናቸው ።

ነገር ግን ለኢንቨስትመንት የዋሉትን  መሬቶች ስንመለከት  ለእርሻ ሰብል ልማት አመቺና በትርፍ አምራችነታቸው የሚታወቁ ናቸው ። ከእርሻ ማሳቸው የተነሱ በርካታ አርሶአደሮችም  ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ አድርጎአቸዋል ።

ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉት የሩቅ ምስራቅ  ሀገራት መካከል ባንግላዲሽን ብንመለከት እንኳን ለኢንቬስትመንት ልማት ያዋለችው መሬት የተራቆተና እጅጉን የተጎዳ መሆኑን የዘርፉ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ  ዳይሬክተሩ ይናገራሉ ።

በሀገራችን የምናየው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው ። ለአምራች ኢንዱስትሪ የዋለው መሬት ለም ከመሆኑም ባለፈ የአርሶ አደሩ የእርሻ ማሳ መሆኑ በዘርፉ ከሚታየው ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑን ነው የተናገሩት።

መንግስት የሀገራችን ኢንቨስትመንት ለማበረታታት የሰጣቸውን አመራጭ ተጠቅመው አምራች ኢንዱስትሪዎች የአካባቢ ጥበቃ ህግንና ደረጃን ሳያሟሉ ወደ ምርት መግባታቸው ሌላኛው የዘርፉ ቁልፍ ችግር ነው ብለዋል።

በ2010 ዓ·ም የአካባቢ ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በፌዴራል ደረጃ ካሉት 55 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በክልሎች በሚገኙ 29 ሺህ የሚሆኑ መካክለኛና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ባካሄደው ጥናት አብዛኛዎቹ ከደረጃ በታች መሆናቸውን  ውጤቱ ያሳያል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣የኬሚካል አጠቃቀምና ማስወገጀ ሥርዓት ሳይዘረጉ በሥራ ውስጥ ያሉ መሆኑን በተደረገው ጥናት  ተረጋግጧል ።

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የአበባ እርሻ ልማት ድርጅቶች ውስጥ ሶስቱ ብቻ የአካባቢ ጥበቃ ህግ ተግባራዊ ያደረጉ ናቸው ያሉት አቶ መሀሪ 28 የሚሆኑት በኬሚካል አያያዝና አወጋገድ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው መሆኑን በጥናት አረጋግጠን አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ አስቀምጠናል ነው የሚሉት።

በኦሮሚያ ክልል በማምረት ላይ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን አላሟሉም ያሉት ደግሞ የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ስንታየሁ በፍቃዱ ናቸው።

በሀገሪቷ ካሉ አጠቃላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች 54 በመቶ የሚሆነው በክልሉ እንደሚገኝ የተናገሩት ሃላፊው ከኢንቨስትመንት መሬት አዘገጃጀትና አሰጣጥ ጀምሮ የአካባቢ ሥነ ምህዳርና ጥበቃን ከግምት ውስጥ ያላስገባ የዘርፉ ልማት ችግሮች እንዳሉበት ያስረዳሉ ።

በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኢንቨስትመንት የተሰጣቸው መሬት የእርሻ ማሳዎች ከመሆኑም ባሻገር የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣የኬሚካሎች አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርዓት ሳይዘረጉ ወደ ምርት መግባታቸው ችግሩ ውስብስብ አድርጎታል ።

ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች፣ኬሚካሎችና ተረፈ ምርቶች ሳይንሳዊ አያያዝ፣አወጋገድ፣የክምችትና ማስወገጃ ቦታ ሳይኖራቸው ወደ ምርት መግባት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ አሁንም የሚታዩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን በተደረገው ቁጥጥር ተረጋግጧል ይላሉ።

በዋናነት የፍሳሽ ቆሻሻዎች የአዋሽ ወንዝን ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ ወንዞች እየተለቀቁ አርሶ አደሩ በሚያመርተው የሰብልና እንስሳት ሀብት ላይ ጉዳት ከማስከተሉም ባለፈ ለዜጎች ጤንነት ጠንቅ እየሆነ መጥቷል ።

የአካባቢው ህብረተሰብ ለውሃ ወለድና ለተለያዩ የቆዳ ካንሰር በሽታዎች ጭምር እየተጋለጠ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ሃላፊው ይናገራሉ።

ችግሩን ለመፍታትና አምራች ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ እያደረግን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጭምር ርብርበ ተጀምሯል ።

ወደ አካባቢ አየር ንብረት ለውጥ በካይ ጋዞች በመልቀቅ በህብረተሰቡ ጤንነትና አኗኗር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ የነበሩት 13 የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች፣ የቆዳ ፋብሪካዎች፣የአበባ እርሻ ልማት ድርጅቶችና የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን መዘጋታቸውን ነው የገለፁት።

በክልሉ በማምረት ላይ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢውና ህብረተሰቡ ጤና አመች እንዲሆኑ ከኢንቨስትመንት መሬት መረጣ ጀምሮ መንግስት ዘርፈ ብዙ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስድ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ የህግና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ፣የኬሚካል አጠቃቀምና አወጋገድ ዘመናዊ አሰራር ተከትለው እንዲሰሩ ቋሚ ኮሚቴው የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሀገራችን ለዜጎች ህይወትና አካባቢ አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆነ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግንባታ እውን እንዲሆን በዘርፉ የተቀመጡ ፖሊሲዎችና የህግ ማእቀፎች በአምራች ኢንዱስትሪዎች በአግባቡ በሥራ ላይ እንዲውሉ ሁላችንም የየድርሻችን መወጣት አለብን  ።

አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚሰማሩበት ዘርፍ እሴትን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ እንጂ ለም የእርሻ መሬትን የሚያመክኑ መሆን የለባቸውም ። ከአካባቢ የአየር ንብረት ጋር የተጣጣሙና የህብረተሰቡን ጤንነት የሚጠብቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚለው የፀሃፊው መልእክት ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም