አቅራቢዎች በአኩሪ አተርና ሽምብራ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል

371

አዲስ አበባ  ጥር 8/2011 አኩሪ አተርና ሽምብራ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት በመግባታቸው አቅራቢዎች ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ተነገረ።

ምርት ገበያው አኩሪ አተርና ሽምብራን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ለማስገባት ካለፈው ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ምርቶቹን በዘጠኝ ቅርንጫፎቹ መቀበል ጀምሯል። ግብይቱ መጀመሩንም ዛሬ በይፋ አስታውቋል።

በውጭ ገበያ ተፈላጊነት ያላቸው የእነዚህ ምርቶች ወደ ዘመናዊው የግብይት ስርዓት መግባት አርሶ አደሮችን፣ አቅራቢዎችንና ላኪዎችን እንዲሁም አገሪቱን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።

የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ እንዳሉት ግብይቱ ለወጪ ንግድ እድገት አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖርና ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲላክ ከማድረግ ባሻገር አቅራቢዎች ግብይት በተፈጸመ ማግስት የምርታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል። 

አቅራቢዎች ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውንና በሁለት ሳምንት ውስጥ ከ29 ሺህ ኩንታል በላይ አኩሪ አተር መቅረቡን፣ በአራት የግብይት ቀናትም ከ2 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ግብይት መፈጸሙን ገልጸዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአኩሪ አተርና የአረንጓዴ ማሾ ግብይት አስገዳጅ ሆኖ በምርት ገበያው ብቻ እንዲከናወን መወሰኑ ግብይቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

ኑግና ባቄላ በጥቂት ወራት ውስጥ የምርት ገበያውን ዘመናዊ የግብይት ስርዓት እንደሚቀላቀሉም ጠቁመዋል።

ምርት ገበያው ተደራሽነቱን ለማሳደግ በቅርቡ በሁመራና በነቀምቴ አካባቢያዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት እንዲሁም በመቱና በቴፒ ቅርንጫፍ እንደሚከፍት አስታውቋል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ 439 ሺህ ቶን ሽምብራ እና 76 ሺህ ቶን አኩሪ አተር በኢትዮጵያ ተመርቷል።

ሁለቱም ምርቶች በዓለም ገበያ ተፈላጊነት ያላቸው ሲሆኑ ባለፈው ዓመት 110 ሺህ ቶን አኩሪ አተርና 49 ሺህ ቶን ሽምብራ ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በኢትዮጵያ ከአኩሪ አተር አጠቃላይ ምርት 99 ነጥብ 6 በመቶው የሚመረተው በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ሲሆን 90 በመቶ የሽብራ ምርት ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ይመረታል።