በፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ነገ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ

66

አዲስ አበባ ጥር 8/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና እና ተከታዩ ሃዋሳ ከተማ በነገው እለት የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል።

የሊጉ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሲካሄዱ ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ነገ ከቀኑ 11:00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በፈረንሳዩ አሰልጣኝ ዲዲየር ጎሜዝ የሚሰልጥነው ኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ በ19 ነጥብ እየመራ ሲሆን በአዲሴ ካሳ የሚሰለጥነው ሃዋሳ ከተማ ደግሞ በ18 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ሃዋሳ ከተማ ደግሞ መሪነቱን ለመረከብ የሚያደርጉት በመሆኑ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ ተጠባቂ ሆኗል።

ሁለቱም ቡድኖች በዘንድሮው የውድድር ዓመት መልካም ጅማሮና ጥሩ ግስጋሴ እያደረጉ ሲሆን የነገው ጨዋታ በቡድኖቹ መካከል ጠንካራና ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያ ቡና እና ሃዋሳ ከተማ ጨዋታ በተጨማሪ ነገ ሶስት ጨዋታዎች በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

በዚሁ መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከባህርዳር ከተማ፣በሃዋሳ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስ ከሲዳማ ቡና እና በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም ፋሲል ከተማ ከወላይታ ድቻ በጎንደር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የጥምቀት በዓል ዝግጅት በስታዲየሙ በመኖሩ ከነገ በስቲያ አርብ ከቀኑ አራት ሰዓት ይካሄዳል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከስሑል ሽረ  ደግሞ አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል።

እሁድ ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደደቢት ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9:00 የሚጫወቱ ይሆናል።

በ11ኛው ሳምንት መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጅማ አባ ጅፋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከሞሮኮው ሃሳኒያ ዩኤስ አጋዲር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ምክንያት በዚህ ሳምንት አይካሄድም።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተስተካካይ መርሃ ግብር የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ  9:00 በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ19 ነጥብ ሲመራ፣ ሃዋሳ ከተማ በ18 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

ስሑል ሽረ፣ ደደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።

የኮከብ ጎል አግቢነቱን የአዳማው ዳዋ ሁቴሳና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 7 ግቦች ሲመሩ፣ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ6 የሀዋሳ ከተማዎቹ እስራኤል እሸቱና ታፈሰ ሰለሞን በተመሳሳይ 5 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም