በአዲስ አበባ ከተማ ትናት ምሽት በደረሰ የእሳት አደጋ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

88

አዲስ አበባ ጥር 8/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት ምሽትና ሌሊት ላይ ሶስት የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የእሳት አደጋ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ።

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጣር ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው 45 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከጥፋት ማዳን ተችሏል።

የእሳት አደጋው የደረሰው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ሳፋሪ ትምህርት ቤት አካባቢ በአንድ የግል ማተሚያ ቤት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መሆኑን ኤጀንሲው ጠቅሷል።

በአደጋው በማተሚያ ቤቱ ላይ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ በሸቀጣ ሸቀጥቅ ሱቅ ላይ 50 ሺህ ብር፣ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ደግሞ 600 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።

ሆኖም 45 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከእሳት አደጋው ማዳን መቻሉን የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ ገልፀዋል።

በአጠቃላይ 10 ያህል የኤጀንሲው ተሸከርካሪዎች በአደጋ መከላከሉ የተሳተፉ ሲሆን 86 ሺህ ሊትር ውኃ ጥቅም ላይ ውሏል። 

የቃጠሎውን መንስኤን በተመለከተ የማተሚያ ቤቱ የኤሌክትሪክ ኮንታክት ችግር፣ በመኖሪያ ቤቱ ከማድቤት የተነሳ እሳት መሆኑን ጠቁመዋል።  

ህብረተሰቡ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድርግ አለበት ያሉት አቶ ስለሺ ተቀጣጣይ ነገሮችን በጥንቃቄ መያዝ እና የኤሌክትሪክ እቃዎችን ከመጠቀም በፊት በባለሙያ መገጣጠምና በአንድ ማከፋፈያ ላይ ብዙ ሶኬትን አለመጠቀም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም