የብሄራዊ መረጃና ደህንነት የመዋቅር ለውጥ ለዜጎች ሰላምና ደህንነት ዋስትና ይሰጣል.. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

81

አዲስ አበባ ጥር 8/2011 የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጀመረው የመዋቅር ለውጥ  ለዜጎች ሰላምና ደህንነት ዋስትና ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ።

ተቋሙ በሩን ክፍት በማድረግ ዜጎች የሚፈሩት ሳይሆን የሚኮሩበትና የሚመኩበት እንዲሆን ተደርጎ እየተደራጀ ነው ተብሏል። 

የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተቋሙ እየተካሄደ ባለው መዋቅራዊ ለውጥና የትግበራ ሪፖርት ላይ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል። 

"በኢትዮጵያ ታሪክ የደህንነት መስሪያ ቤቱ በግልጽ ስራውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያው ነው" ሲሉ ነው  የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ የገለፁት።

ተቋሙ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበርና የህዝብ ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ዜጎች እምነት የሚጥሉበት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን መገንዘባቸውንም ሰብሳቢው አክለዋል።

የተቋሙ አመራርና ሰራተኛ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ነፃና ገለልተኛ በመሆን ለትውልድ የሚተላለፍ የህዝብ ደህንነት ጠባቂ ተቋም ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ማንኛውም ዜጋ የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረጋቸው፤ ጉዳይ አለኝ የሚል ተገልጋይ እስከ ዋና ዳይሬክተሩ በመዝለቅ መወያየት የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱንም አድንቀዋል።

በቀጣይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግና ስርዓቱን ተከትሎ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስፈላጊውን ድጋፍ፣ ክትትል፣ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል  አደም መሀመድ እንዳሉት፤ ተቋሙን ገለልተኛና ነፃ በሆኑ ብቁ ባለሙያዎች በመምራት የሀገርና ዜጎችን ደህንነት ለመበቅ የሚያስችል ለውጥ እየተደረገ ነው።

ተቋሙ ባለፉት ዓመታት በህግ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር ውጭ ዜጎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማሰርን፣ ማሰቃየትንና ከሀገር እንዳይወጡ ማገድን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀሙ እንደነበር አንስተዋል።

እንደጀነራል ዳይሬክተሩ ገለፃ ከ1986 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያት ለተቋሙ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ ወደ ሀገር እንዳይገቡና ወደ ውጭ እንዳይወጡ የተደረጉ ከ2 ሺህ 600 በላይ ዜጎች እግድ ተነስቷል።

የሰው ሀይል አስተዳደር ደንብና መመሪያ ባለመኖሩ እስካሁን ከ180 በላይ የተቋሙ ሰራተኞች "ያለ አግባብ ተባረናል" በሚል ቅሬታ አቅርበው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።

በተቋሙ ከ20 ዓመት በላይ ያገለገሉ ባለሙያዎች ቢኖሩም 87 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት ዝግጅታቸው ዲፕሎማና ከዲፕሎማ በታች መሆኑን ገልጸዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበለጸገ ለማድረግ በዘርፉ የበቁ ባለሙያዎችን ማምጣት የሚያስችል አደረጃጀት እየተዘረጋ  እንደሆነም ነው ጀነራል አደም የተናገሩት። 

አክለውም "ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ለሁሉም ዜጎች በሩን ክፍት በማድረግ ዜጎች የሚፈሩት ሳይሆን የሚኮሩበትና የሚመኩበት እንዲሆን በገለልተኛና በሙያው ብቃት ባላቸው ሰዎች እየተደራጀ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤቶች ታሪክ አንዱ ሲገነባ ሌላው በማፍረስ የተመሰረተ መሆኑን ያመለከቱት ጀነራል አደም፤ የአሁኑ አደረጃጀት ግብ "በወቅቱ ያለውን መንግስት ወይም ስርዓት ማገልገል ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ አደረጃጀት መፍጠር ነው" ሲሉም አብራርተዋል።

ለዚህም የዜጎችንና ሀገርን ደህንነት በማረጋገጥና ሚስጥር በመጠበቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ ነው የሚለውና የሚወደው ተቋም እንዲሆን በነጻና ገለልተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተደራጀ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ከግንቦት ወር ጀምሮ ከ32 ሺህ በላይ ከከባድ እስከ ቀላል የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ጠቅሰዋል።

በቁጥጥር ስር እየዋሉ ካሉት የጦር መሳሪያዎች መካከል አብዛኛው ሽጉጥ የቱርክ ሪት በመሆኑና የሚገባውም በሱዳን በኩል በመሆኑ ዝውውሩን ከምንጩ ለማጥፋት ከቱርክና ሱዳን መንግስታት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለጦር መሳሪያ ግዥ አገልግሎት ሊውል ይችል የነበረ ሁለት ሚሊዬን ዶላርን ጨምሮ ሌሎች ገንዘብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ሊወጣ ሲል ተይዟል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማጥናት ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ በዜጎች ላይ ሊደርስ  ይችል የነበረ አደጋ እንዲቆም መደረጉንም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር  ገልፀዋል።

በተለይም ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩት ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና በሌሎች አካባቢዎች ችግሩን ለማባባስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላትን መረጃ በመተንተን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በኩል የተቋሙ ሚና የጎላ እንደነበርም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም