የአማራና የትግራይ ክልሎች መሪዎች ለህዝቦቻቸው ሠላምና መረጋጋት ተግተው ለመስራት ቃል ገቡ

64

አዲስ አበባ ጥር 8/2011 የአማራና የትግራይ ክልሎች መሪዎች ለህዝቦቻቸው ሠላምና መረጋጋት ተግተው ለመስራት ቃል ገቡ፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ ህብረትና የአገር ሽማግሌዎች ከህዳር 18 ጀምሮ ላለፉት ተከታታይ ስድስት ሳምንታት በአገሪቱ አራት ክልሎች ተዘዋውረው ከህዝብና ከአመራሮች ጋር ተወያይተው ነበር።

በአገሪቱ ከዚህ ቀደም የነበረው የሰላም፣ የአብሮነት እና የመቻቻል እሴት እየተሸረሸረ የመምጣት ምልክቶች እየታዩ በመምጣታቸው ይህን ሁኔታ ለመቀየር የኃይማኖት መሪዎቹና የአገር ሽማግሌዎቹ በክልሎች የሰላም ጉዞ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በዚህም በትግራይ፣ በአማራ፣ አሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ተዘዋውረው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና አመራር አካላትን አወያይተዋል።

በተለይም በትግራይ እና አማራ ክልሎች አሁን ላይ እየታየ ያለው ችግር የህዝቡ ሳይሆን የአመራር መሆኑን ህብረተሰቡን ባወያዩበት ወቅት መገንዘባቸውን ጠቁመዋል።

በዚህ መሰረትም የሁለቱን ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች አቀራርበው አወያይተው፣ መሪዎች ለህዝቦቻቸው ሠላምና መረጋጋት ተግተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ትናንት ምሽት በሂልተን ሆቴል የማጠቃለያ መድረክ በተካሄደ ሥነሥርዓት ላይም ሁለቱ አመራሮች የገቡት ቃል እንደ ፊርማቸው እንደሚቆጠርም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የሃይማኖት አባቶች በሁለቱ ክልሎች ተዘዋውረው ህዝቡን በማነጋገር በህዝቦች መካከል ምንም ችግር እንደሌለና ሠላም ወዳድ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ መሪዎች ሠላምን በመፍጠር በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ህዝቡ በመግለፁም ይሄ መርሃ ግብር ሊዘጋጅ መቻሉም ተገልጿል፡፡

በዚሁ ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደተናገሩት፤ ሁለቱ ህዝቦች የጋራ ባህል፣ ወግና እሴት ያላቸው መሆኑን አንስተው ማንኛውም ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይሰራል፡፡

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የፖለቲካ አመራሮች ያልሰሩትን የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በመሥራታቸው አመስግነዋል።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች መልካም እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠው አመራሩ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋልዋል፡፡

ዶክተር ደብረጽዮን ፖለቲካውን በማቆየት ሰላምን ማስቀደም እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአማራና ትግራይ ክልሎች ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክሩ ጉዳዮች በማህበራዊ ሚዲያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይራገባል።

የክልሎቹ ከፍተኛ ኃላፊዎች በዚህ ደረጃ ተቀራርበው መነጋገራቸው ችግሩን ለመፍታት የላቀ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም