በ11 የቆዳ ፋብሪካዎች የእግድና ማስጠንቀቂያ እርምጃ ተወሰደባቸው

87

አዲስ አበባ ጥር 8/2011የተረፈ ምርት አወጋገዳቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍና ክትትል ቢደረግላቸውም ያላስተካከሉ 11 የቆዳ ፋብሪካዎች የእግድና የማስጠንቀቂያ እርምጃ ተወሰደባቸው።

የደን፣ አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የተረፈ ምርት አወጋገድ ችግር ባለባቸው ፋብሪካዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እንደሚያጠናክር አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ሞጆ በሚገኙት ቆዳ ፋብሪካዎች ላይ የእግድና የማስጠንቀቂያ እርምጃ የወሰደው ከኦሮሚያ ክልል ደን፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ነው።

ፋብሪካዎቹ በ1995 ዓ.ም የጸደቀውን የአካባቢ ብክለት መከላከል አዋጅና በ2001 ዓ.ም የወጣውን የማስፈፀሚያ ደንብ እንዲተገብሩ የአምስት ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ሶስት ፋብሪካዎች ተረፈ ምርታቸውን አጣርተው በማስወገድ ረገድ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ቢገኙም አሁንም የሚቀራቸው ስራ መኖሩን ምክትል ኮሚሽነሯ ፍሬነሽ መኩሪያ ተናግረዋል።

ሌሎች አራት ፋብሪካዎች ተረፈ ምርታቸውን በከፊል አጣርተው የሚያስወግዱ ሲሆኑ ቀሪዎቹ አራት ደግሞ ምንም ሳያጣሩ ወደ ወንዝ የሚለቁ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በመሆኑም ተረፈ ምርታቸውን ምንም ሳያጣሩ ወደ ወንዝ የሚለቁት ፋብሪካዎች በ15 ቀን ውስጥ የጀመሩትን ምርት ጨርሰው እንዲታሸጉ ተወስኖባቸዋል።

ተረፈ ምርታቸውን በከፊል የሚያጣሩት አራት ፋብሪካዎችም ስራ ሳያቆሙ የማጣራት አቅማቸውን እንዲሟሉ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

ቀሪዎቹ ሶስት ፋብሪካዎች 'ችግር የለብንም' ቢሉም ማጣራት ተደርጎ በሶስት ወር ውስጥ ውጤቱ እንዲቀርብ መታዘዙን ምክትል ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

እንዲዘጉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ፋብሪካዎች ችግራቸውን ሳይፈቱ ስራ የማይጀምሩ ሲሆን ሰራተኞቻቸው ግን ደመወዛቸው እንማይቋረጥባቸው ተነግሯል።

የኦሮሚያ ክልል የደን፣ የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ ፈቃዱ በውጭ አገር ባለሃብቶች የተቋቋሙት አብዛኞቹ ፋብሪካዎች ለአካባቢ ብክለትና አየር ንብረት ለውጥ መከላከል አዋጅ ተፈፃሚነት ትኩረት አለመስጠታቸውን ነው የተናገሩት።

የትኩረት ማጣታቸው ዋነኛው ምክንያትም እንደ አገር ፋብሪካዎችን ማስፋፋት ላይ ብቻ 'ማተኮራችን ነው' ብለዋል።

በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ ችግር ስለሚታይባቸው ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም