አባገዳዎች ያመቻቿቸው የሰላም ውይይቶች ውጤት እያስገኙ ነው

69

ነገሌ ጥር 8/2011 በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች የነበሩ አለመግባባቶች በሰላም እንዲፈቱ ያመቻቿቸው የሰላም ውይይቶች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ ሚጠጋ ኖቴ  ገለጹ፡፡

አባገዳው እንዳሉት ውይይቱ  የተካሄደው በሁለቱ ዞኖች ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ አባላት ከህዝብ ጋር ጭምር ነው፡፡

በዞኖቹ ጥላቻና  ቂም በቀል ቀርቶ አለመግባባቶች በድርድርና በውይይት ብቻ እንዲፈቱ በባህላዊ የገዳ ስርዓት አቅጣጫ መቀመጡንና የሰላም ሳምንት መታወጁን አስታውሰዋል፡፡

የሰላም ሳምንቱ በኦሮሞ ባህል መሰረት የተጣላ የሚታረቅበት ፣የበደለ የሚካስበት፣  የይቅርታና የእርቀ ሰላም እንደሆነ  አባገዳ ሚጠጋ አስረድተዋል፡፡

በዞኖቹ መሳሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የኦነግ አባላት ከውይይቱ በኋላ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስነው እየተመለሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አባገዳ ሚጠጋ እንዳሉት በአካባቢዎቹ  አልፎ አልፎ  የነበረው ግጭት መቀነሱንና በአሁኑ ጊዜ የአካባቢዎቹ ህብረተሰብ  በሰላም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

"ይቅር መባባሉ የህግ የበላይነትን አክብሮ በማስከበር ለሀገሪቱ ገጽታ ግንባታ ተባብሮና ተረዳድቶ በመስራት ሁሉም የድርሻቸውን ለመወጣት ነው" ብለዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች ፣የኃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች ልምዳቸውን በማካፈል ስለ ሰላም እያስተማሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የፖለቲካ  ፓርቲዎችም ለደጋፊዎቻቸው መልካም መልካሙን በማስተማር ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ገጽታ ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ መክረዋል፡፡

ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ለአንድ ለተወሰነ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉንም የሚያሳስብ የጋራ ጉዳይ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ሰሞኑን የተካሄዱት ውይይቶቹ በምዕራብ ጉጂ ዞን ዱግዳዳዋ  እና  ቡሌ ሆራ ከተሞችን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ሲሆን በምስራቅ ጉጂ ደግሞ አዶላ፣ ሻኪሶ፣ ሰባቦሩ፣ ዋደራ እና አጋ ዋዩ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

በውይይቶቹ  ቅሬታ አለን የሚሉትን ወገኖች ጨምሮ አባገዳዎች የኃይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

ተመሳሳይ ውይይቶች እንደሚቀጥሉም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም