የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የጌዴኦ ዞን አመራሮች ገለፁ

52

ዲላ ጥር 8/2011 በጌዴኦ ዞን የሕግ የበላይነትን ለማስፈን በሚከናወኑ ተግባራት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ የዞኑ አመራሮች ገለፁ፡፡

አመራር አካላቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና የሕግ የበላይነትን አስመልክቶ በዲላ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ከተወያዮቹ መካከል የዲላ ከተማ ደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ንኡስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ምስጋና ዋቃዮ የህዝቡን ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚሰራበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዲላ ከተማ በሚስተዋለው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የመንግስት ሠራተኞች ጭምር በአመቻችነት እንደሚሳተፉ ገልጸው ይህም በአካባቢው አልፎ አልፎ ለሚስተዋሉ ግጭቶች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በሀገር ደረጃ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው በዲላ ከተማ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በከተማውም ሆነ በዞኑ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና አሁን ያለው ሠላም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡

በአጎራባች ዞኖች ያሉ የፀጥታ ችግሮች ሥጋት ቢሆኑም የጌዴኦ ዞን አንፃራዊ ሠላም ያለበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቡሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተከተል አበራ ናቸው፡፡

አልፎ አልፎ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር ፀብ የብሔር መልክ እንዲይዝ በማድረግ ሁከት ለመፍጠር የሚረባረቡ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

"በከተሞች አካባቢ እየተበራከተ የመጣው ዝርፊያና ንጥቂያም ለነዋሪዎች ሥጋት እየሆነ ያለ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው" ያሉት አቶ ተከተል፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን አመራሩንና ህብረተሰቡን አስተባብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በበኩላቸው "ሕግ ጉልበት የሚኖረው ህግን እንዲያስከብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ህጉን ሲያከብሩና ማስከበር ሲችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በፍትህ አካላት ላይ በተሰሩ የማሻሻያ ሥራዎች ለውጦች ቢመጡም አሁንም የሕዝብን እርካታ በሚፈለገው ልክ መፍጠር አልተቻለም።

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለፃ በመርማሪ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግና ዳኞች ላይ ከብቃት ማነስ ችግር በተጨማሪጫፍ የወጣ የሥነ-ምግባር ጉድለት ይታያል ፡፡

በዞኑ የህግ የበላይነትን ለማስፈን ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ ተቀናጅተው እንዲሰሩም ትኩረት እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም