በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታ ተጠየቀ

66

አምቦ ጥር 8/2011 በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ  የተፈጠረው ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታ መንግስትና ኦነግ ተቀራርበው ለዘላቂ ሰላም እንዲሰሩ የአምቦ ከተማ ወጣቶች ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ።

ከትምህርት ቤቶችና ከሌሎችም የከተማው አካባቢዎች ተሰባስበው ሰልፍ ያካሄዱት  እነዚህ ወጣቶች ለችግሩ አፋጣኝ እልባት እንዲሰጠው ባሰሟቸው መፈክሮችና በሰጡት አስተያየት ነው ጥያቄውን ያቀረቡት፡፡

በደም የተገኘው አንድነት ሲፈርስ ቁጭ ብለን አንመለከትም፣  በመንግስትና ኦነግ መካከል የተደረገው የአስመራ ስምምነት ለህዝብ ይፋ ይሁን፣ ኦነግ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ  ወደ ታገለለት ህዝብ ይቀላቀል፣ ግጭት በአፋጣኝ ይቁም ወጣቶቹ ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል ይገኙበታል፡፡

የኦሮሞ ፓርቲዎች እውነት ለህዝቡ የሚታገሉ ከሆነ እርስ በርስ መበላላቱን ትተው ለህዝቡ ሰላም ተስማምተው መስራት እንዳለባቸው ያመለከቱት ወጣቶቹ " ድርጅታችን ህዝባችን ነው፣የውሸት ፕሮፖጋንዳ ይቁም፣ኦሮሞ አንድ ነው " በማለት ድምጽቸውን አሰምተዋል፡፡

ዓላማቸው ትምህርት እንጂ ሁከትና ብጥብጥ እንደማይፈልጉም አመልክተዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ  ግድያ ፣  መፈናቀልና  ዝርፊያ  እንዲያስቆሙ ለፌዴራልና ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከሰልፈኞቹ  መካከል ወጣት ዱፌራ ማሞ  እንዳለው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በህዝብና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዳሳሰበው ተናግራል።

" መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር እየጠፋ ያለውን ሕይወትና ንብረት ማስቆም አለበት"  ብሏል።

ተማሪ ጀማነህ በላይ በበኩሉ  ግድያ የፈጸመውና ንብረት በማውደም ዘረፋ ያካሄዱትን ለይቶ በአፋጣኝ ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡

"በቸልተኝነት የሚታለፉ ጥፋቶች ሕዝብን ለሞትና ለስደት ስለሚዳርጉ ከወዲሁ አፋጣኝ መፍትሄ ሊፈለግለት  ይገባል" ብላል ።

መንግሥት ግጭትን በሀገር ሽማግሌዎች፣ በገዳ ሥርዓትና በሌሎችም ባህላዊ የዕርቀ ሰላም አማራጮች እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባው የጠቆመው ደግሞ የአምቦ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሊኪሳ ከበደ ነው፡፡

በአምቦ ከተማ የተካሄደው ይሄው ሰልፍ በሰላም  መጠናቀቁን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግባለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም