የአማራና ትግራይ ክልል አመራሮች ለሁለቱ ህዝቦች ሠላምና ደህንነት ተግተው ለመሥራት ቃል ገቡ

1006

አዲስ አበባ  ጥር 7/2011 የኢትዮጵያ ሃይማኖቾች ጉባኤ ህብረትና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የተካሄደ ሥነሥርዓት ላይ የአማራና የትግራይ ክልል መሪዎች ለህዝቦቻቸው ሠላምና መረጋጋት ተግተው እንደሚሰሩ  ቃል ገብተዋል፡፡

ዛሬ ማምሻውን  በሂልተን ሆቴል በተካሄደ በዚህ ስነስርዓት ላይ ሁለቱ አመራሮች የገቡት ቃል እንደ ፊርማቸው እንደሚቆጠርም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የሃይማኖት አባቶች በሁለቱ ክልሎች ተዘዋውረው ህዝቡን በማነጋገር በህዝቦች መካከል ምንም ችግር እንደሌለና ሠላም ወዳድ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ መሪዎች ሠላምን በመፍጠር በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ህዝቡ በመግለፁም ይሄ መርሃ ግብር ልዘጋጅ መቻሉም ተገልጿል፡፡

በዚሁ ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደተናገሩት ሁለቱ ህዝቦች የጋራ ባህል፣ወግና እሴት ያላቸው መሆኑን አንስተው ማንኛውም ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይሰራል ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የፖለቲካ አመራሮች ያልሰሩትን የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በመሥራታቸው ምስጋና አቅርበው፤ የሁለቱ ክልል ህዝቦች መልካም እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡