የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የቀረቡላቸውን የመፍትሔ አማራጮች ባለመቀበላቸው ከከተማው እንዲወጡ ተጠየቀ

100

ባህርዳር ጥር 7/2011 ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በመውጣት በባህር ዳር ከተማ የተጠለሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ለቀረቡላቸው አማራጮች ከመስማማት ይልቅ የጸጥታ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ ከተማውን ለቀው እንዲወጡ የከተማው ከንቲባ አሳሰቡ።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች የከተማው ህዝብ ባደረገላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ከታህሳስ 19/2011 ዓ.ም ጀምሮ በከተማው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የከተማው ህዝብና ወጣቶች የመኝታ ፍራሽ፣ የምግብ አቅርቦትና አልባሳትን በመደገፍ ያልተቆጠበ ወንድማዊ ድጋፍ ቢያደርግም ከትናንት ጀምሮ ከተጠለሉበት በመውጣት የከተማውን ጸጥታ እያወኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በዛሬው እለትም ተመሳሳይ ሁከት በመፍጠር የቱሪዝም ከተማ የሆነችውንና በሰላማዊነቷ የምትታወቀውን የባህር ዳር ከተማ ሲረብሹና ጉዳት ሲያደርሱ ውለዋል"ብለዋል።

"ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረስ፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲዘጉና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎልም አድርገዋል"ብለዋል።

ችግሩ በመባባሱ የከተማው ሰላም እየታወከ በነዋሪዎችና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት መቀጠል ስለሌለበት ከተማውን ለቀው ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረው የከተማው ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ላደረጉት የማረጋጋት ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዘውዱ ዘለቀ በበኩላቸው "ተማሪዎቹ  ከከተማው አልፈው በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ፣ ፖሊና ሰላም ካምፓሶች በመግባት ረብሻ እንዲፈጠር አድርገዋል"ብለዋል።

ከባህር ዳር ከተማ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ስምንት በመኪና የተጫነ እህል በማራገፍ፣ ተሽከርካሪዎችን በመስበር፣ ቤቶችን በመደብደብ ከተማረ ሰው የማይጠበቅ ተግባር መፈጸማቸውንም አመልክተዋል።

ተማሪዎቹ ጩቤ፣ የጭስ ቦንብ፣ የአደጋ መከላከያ ሄል ሜትና ዱላ ጭምር በመያዝ አደጋ መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከከተማው ሰላም ፈላጊ ወጣቶች ጋር በመተባበር ያለምንም ሰብአዊ ጉዳት እንዲረጋጋ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል።

"አሁን ላይ ለከተማዋ የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሆናቸው ከህዝቡ ጋር በመሆን የክልሉ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ ለመሸኘት ስራ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ተማሪዎችን ለማግባባትና መፍትሄ ለመስጠት በከፍተኛ አመራሩ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም የቀረበላቸውን አማራጭ ባለመቀበል መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ገደቤ ሃይሉ ናቸው።

ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ አለበለዚያ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ባለመስማማት በዛሬው እለት በሃይል በመጠቀም በአካባቢው የከፋ ችግር ለመፍጠር መሞከራቸውን ጠቁመዋል።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ችግራቸው እስኪፈታ በጊዜያዊነት በባህርዳር ከተማ መጠለላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም