"ቻያ" የተሰኘ ጎመን መሳይ ተክል ለምግብነት እንደሚውል በምርምር ተረጋገጠ

84

ድሬዳዋ ጥር 7/2011 "ቻያ" የተሰኘ ጎመን መሳይ ተክል ለምግብነት ሊውል እንደሚችል በምርምር ማረጋገጡን የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ የምርመር ወጤቱ ይፋ በተደረገበት ስነ -ስርዓት ወቅት  እንደተናገሩት ተክሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ "ቶኒ ፋርም" የእርሻ ምርምር ጣቢያ ተፈትሾ ለምግብነት መዋል እንደሚቻል ተረጋግጧል።

ተክሉ ከ50 ዓመት በፊት ከሜክሲኮ የመጣና ያለ ጥቅም ሲባክን የነበረ መሆኑን አስታውሰው ተክሉ በጥሬው ሳይሆን ተቀቅሎ ለሰዎች ምግብነት መዋል እንደሚችል ነው ያስታወቁት።

ተክሉ ከቆስጣና ከጎመን የበለጠ የምግብ ንጥረ ነገር በውስጡ እንደሚገኝ መረጋገጡን የገለፁት ደግሞ የፕሮጀክቱ  አስተባባሪና  ተመራማሪ    አቶ ዳንኤል አለሙ ናቸው፡፡

"ተክሉን ብቻውን በመቀቀል እንዲሁም ከእንቁላል፣ ከሥጋ፣ ከሽሮ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ ባህላዊ ምግብነት ከሚታወቀው "ላፊሶ" ጋር በማዋሀድ ለምግብነት መጠቀም ይቻላል" ብለዋል ።

የምርምረሩ ፕሮጀክት   አባል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዋሱ መሐመድ በበኩላቸው የተክሉ ቁርጥራጭ በተተከለ በሶስት ወራት ውስጥ ቅጠል አፍርቶ ለምግብነት መዋል እንደሚችል አስረድተዋል።

ተክሉ ለኢትዮጵያ አየር ንብረት ተስማሚና ድርቅን መቋቋም የሚችል በመሆኑ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በምርምር ማዕከሉ የተተከለው ብዛት ያለው ችግኝ ለድሬዳዋና ለሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮዎች ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል " ብለዋል ።

ዝናብ አጠር ለሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚሰራጭም አመላክተዋል ።

የድሬዳዋ የግብርና ጽህፈት ቤት ተወካይ  አቶ ሸምሸዲን አህመድ ተክሉ ዝናብ አጠር ለሆኑና የምግብ ዋስትናቸውን ላላረጋገጡ አርሶ አደሮች በምግበነቱ  የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

"በአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያ ገበቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል" ብለዋል ።

የሐረሪ ክልል የግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አዱኛ በበኩላቸው ተክሉ በደረቅ ወቅት  ጭምር በቀላሉ መብቀሉ የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አማራጭ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም