ኦቢኤን በጉጂ ዞን የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት ለመጀመር የሚያስችለውን ግንባታ ሊያከናውን ነው

60

ነገሌ ጥር 7/2011 የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ/ ኦቢኤን/ በ 30 ሚሊዮን ብር በጉጂ ዞን የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት ለመጀመር የሚያስችለውን ግንባታ ሊያከናውን ነው፡፡

በኦቢኤን የጉጂ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጂግሳ ተክሌ እንዳሉት ገንዘቡ ለጽህፈት ቤትና ለስቱዲዮ ግንባታ፣ ለመሳሪያ ግዥና ለውስጥ ድርጅት ማሟያ  የሚውል ነው፡፡

"ከተያዘው  ወር ጀምሮ በዞኑ ነገሌ ከተማ የዘመናዊ ስቱዲዮ ግንባታ ስራ ይጀመራል ''ብለዋል፡፡

የስርጭት አድማሱን ለማስፋት ድርጅቱ የስቱዲዮ ግንባታ ስራውን ለማከናወን የውል ስምምነት የተፈራረሙት የደጉ ከተባለ ሀገር በቀል የግንባታ ተቋራጭ ጋር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በውሉ መሰረት የስቱዲዮ ግንባታ ስራው በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ሰኔ ወር 2011ዓ.ም. የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት እንደሚጀምር ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሬዲዮ ስርጭት ማስተላለፊያ መሳሪያ ግዥ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ለመቅጠር በቅርቡ የምልመላና መረጣ ስራ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያው ስርጭት ሲጀመር በጉጂ ዞን ሶስት ዋና ዋና ከተሞችና በ14 ወረዳዎች ተደራሽ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የተቋራጩ ድርጅት አስተባባሪ ኢንጂነር ደንቦቢ ጥላሁን በበኩላቸው "የስቱዲዮውን ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ ባነሰ ፍጥነትና ጥራት ሰርቶ ለማጠናቀቅ ጥረት እናደርጋለን "ብለዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ነዋሪው  አቶ ጡላ ዱቤ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ከፋና ብሮድካስትና ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጭ ተጨማሪ ጣቢያ እንደማይደርሳቸው ተናግረው የስርጭቱ መጀመርና ተደራሽ መሆን መረጃ ለመስጠትና ለማግኘት እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሀጂ ቁጣ  በበኩላቸው ለአርብቶ አደሩ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መረጃ ለማግኘት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭቶች ተደራሽነት ውስን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

 አዲሱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ስርጭት ህዝቡን በራሱ ቋንቋ ለስራ በማነሳሳት በመቀስቀስና በማስተባበር እንደሚጠቀሙበት ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም