የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ አወንታዊ ለውጥ ማምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ

73

አዲስ አበባ ጥር 7/2011 በአዲስ አበባ በ42 ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የምገባ ፕሮግራም በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ አወንታዊ ለውጥ ማምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ።

በእናት ወግ ማህበር አማካኝነት የሚከናወነው የምገባ ፕሮጀክት ባለፉት አራት ዓመታት ያመጣውን ለውጥ በተመለከተ በኢት አለም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ የንግድ ድርጅት በተሰራው ጥናት ላይ ውይይት ተካሂዷል።

ጥናቱን ያካሄደው ኢት አለም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ የንግድ ድርጅት ባልደረባ አቶ ተድላ አበበ እንደገለጹት የምገባ ፕሮግራሙ በተማሪዎቹ የትምህርት አቀባበልና ተክለ ሰውነት ላይ አወንታዊ ለውጥ አምጥቷል።

የተማሪዎች ዓመታዊ ውጤት ከ62 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 70 በመቶ፣ ምዝገባ በ9 በመቶ፣ የአካል እድገታቸው 21 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ እንዲልና ተመጣጣኝ ክብደት እንዲኖራቸው አስችሏል።

እንደ አቶ ተድላ ገለፃ የተማሪዎችን መጠነ የትምህርት ማቋራጥን በ64 በመቶና በምግብ ምክንያት ከትምህርት ቤት የሚቀሩትንም በ59 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል።

በምገባ ፕሮግራሙ ላይ አገልግሎት በመስጠት የሚሳተፉ ሴቶች በአንድ ተማሪ 14 ብር ክፍያ እንዲያገኙ በማድረግ  ገቢና ቁጠባ እንዲኖራቸው አድርጓል።

በቀጣይ የምገባ ፕሮግራሙ ዘላቂነት እንዲኖረውና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በቂ በጀት መመደብና ለፕሮግራሙ ተመዝግበው የሚጠባበቁ ተማሪዎችን በፕሮግራሙ ማካተት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በቂ ቦታ ያላቸው ትምህርት ቤቶች የግብርና ምርቶችን እንዲያመርቱ ማድረግና  በተመሳሳይ ዘርፍ ከተሰማሩ ማህበራት ጋር በቅንጅት የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻችትም ያስፈልጋል ብለዋል።

የእናት ወግ ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ደብረወርቅ ደበበ በበኩላቸው" ማህበሩ ለተማሪዎች ከሚሰጠው የምገባ ፕሮግራም ባሻገር የቁሳቁስና አሰፈላጊ ድጋፍ በማድረጉ በተማሪዎቹና በተማሪ ቤተሰቦቻቸው ላይ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል" ብለዋል።

የምገባ ፕሮግራሙ በተማሪዎቹ ላይ ካመጣው የትምህርትና የአካል ማሻሻል በተጓዳኝ በስነ-ልቦና እና በጤናቸው ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል ነው ያሉት።

የማህበሩ የበላይ ጠባቂ የቀድሞ ቀዳማይ እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ደግሞ በተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የሚሳተፉ ተማሪዎች ወጥ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

ለዚህም መንግስት ፕሮጀክቶቹን ወስዶ የአመጋገብ ደረጃ በማውጣት በበላይነት የሚያስተዳድርበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የምገባ ደረጃ ባለመኖሩ በትምህርት ቤቶች የተለያየ ዓይነት የአመጋገብ ስርዓት እንደሚስተዋልም ወይዘሮ ሮማን ተናግረዋል።

የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚያስተምሩ ከአንድ ሺህ በላይ ሴት መምህራን በ2006 ዓ.ም የተቋቋመ ማህበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም