ቴክኖሎጂን ማእከል ያደረገ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴ በኢትዮጵያ በዝቅተኛ ደረጃ ያለ መሆኑ ተገለጸ

82

አዲስ አበባ ጥር 7/2011 በሌላው ዓለም በስፋት በመተግበር ላይ ያለውና ቴክኖሎጂን ማእከል ያደረገ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴ በኢትዮጵያ ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ።

ይህም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲተገበር በመሰራት ላይ ያለውን የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርአት ለመተግበር በግብይት ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች ውይይት አካሄደዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ  በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አዲሱ ትውልድ ለስራ ፈጠራና ለሀብት ማፍሪያ እምቅ አቅሙን ለመጠቀም የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞችን ማልማትና የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓትን መተግበር ቅድሚያ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

ቴክኖሎጂ የሚለማባቸውን ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠርም ለወጣት የቴክኖሎጂ በልጻጊ ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ የፋይናንስ ድጋፍ ማእቀፎችን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉን ለማበረታታት ደግሞ ወሳኝ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ማሻሻል ተገቢ እንደሆነም ነው የሚናገሩት፡፡

ሰሞኑን ይፋ የሆነውና 'ሼባ ቫሊ 2018 ቴክ ስታርት አፕ ፈንዲንግ ኢን አፍሪካ' በሚል ርእስ በአይቤክስ ዳይጀስት የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በ2018 እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በአፍሪካ ለቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች በተደረገ ድጋፍ ኬንያ በ156 ሚሊዮን ዶላር አንደኛ ደረጃ ስትይዝ ኢትዮጵያ በ13 ሚሊዮን ዶላር በሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ይህ ደግሞ እንደሀገር ቴክኖሎጂን የእድገታችን አንዱ ምሰሶ አድርጎ በመገልገሉ ረገድ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩን ያመላክታል።

በተለይም የአገልግሎት ዘርፉን ከኤሌክትሮኒክስ ግብይትና ኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ውጭ ለይቶ ማሰብ እንደማይቻል ያሳያል።

በ2015 በተደረገው አንድ ጥናት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ብቻውን 296 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጥቅም ያስገኘ ሲሆን ይህም በአማካይ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ስራዎችን በየዓመቱ ከመፍጠር ጋር በእኩል እንደሚታይ ነው ጥናቱ የሚያሳየው።

የክሬዲት ካርድ፣ ዴቢት ካርድ፣ ኢ-ዋሌት፣ የባንክ የማስተላለፍ ዘዴና የካሽ ክፍያ ዘዴ የሚባሉት ደግሞ የዚህ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ዘዴዎች ሲሆኑ አገራችን በዚህ ዘርፍ እጅግ ወደ ኋላ ከቀሩት ዓለማት እንደሚትመደብ ነው ጥናቱ ያመላከተው።

ይህን ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ብዙ መሰራት እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል።

ዓለማችን 79 ትሪሊየን አጠቃላይ ዓመታዊ ሀብት የምታመነጭ መሆኑን የገለጸው መረጃው፤ ከዚህም ውስጥ ስድስት ትሪሊዬን ዶላር የሚመነጨው በቴክኖሎጂ ብቻ ነው፡፡ ይህም በየዓመቱ 18 ትሪሊዮን ከምታመነጨው አሜሪካና 11 ትሪሊዮን ከምታመነጨው ቻይና ቀጥሎ ሶስተኛው ግዙፍ የኢኮኖሚ አገረ ያደርገዋል።

ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ያለው ትልቁ የኢኮኖሚ እድገት ልዩነት ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀምና ባለመጠቀም መካከል ያለ ልዩነት ብቻ በመሆኑም ቴክኖሎጂ ለእድገት ዋልታ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም