የእምቦጭ አረምን ለመከላከል ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

57

ጋምቤላ ጥር 7/2011 በጋምቤላ ክልል በተለያዩ የውሃማ አካላት ላይ እየተስፋፋ ያለውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል ህብረተሰቡ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡

በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ በአንድ መለስተኛ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በህዝቡ ተሳትፎ የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

በዚህ ወቅት የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ እንደተናገሩት የእምቦጭ አረም በክልሉ በሚገኙ ኩሬዎች ፣ሀይቆች፣ ባሮን ወንዞችና በሌሎችም የውሃ አካላት ላይ  ተስፋፍቶ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

በተለይም አረሙ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በሚገኘው መለስተኛ ሐይቅ ላይ በመከሰት በሐይቁ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

ሐይቁ በአካባቢው ለሚገኙ አምስት የመንደር ማዕከላት ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚውል ጠቁመው በዚህም ህብረተሰቡ በበጋ ወራት ውሃ ፍለጋ ወደ ወንዞች አካባቢ ይሄድ የነበረውን በመተው በቋሚነት መኖር እንደጀመረ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በሐይቁ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ተስፋፍቶ  ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ለህብረተሰቡ ስጋትና  ጫና መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡

የእምቦጭ አረሙ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በበጋው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ አረሙን የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ በተለይም አረሙን በመከላከል እያሳየ ያለው ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው ቢሮው አረሙን ለመከላከል እያደረገ ላለው ጥረት መሳካት የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጠናከርም  ጠይቀዋል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር የእምቦጭ አረሙን ሲያስወግዱ የነጋገራቸው የአካባቢ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሐይቁ በመኖሩ ለከብቶቻቸው፣ ለንጽህና መጠበቂያና ለዓሳ ምርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ካንግ ኛክ  እንዳሉት  ሐይቁ በእምቦጭ ከመሸፈኑ በፊት ለከብቶቻቸው፣ ለዓሳ ማስገርና ለሌሎችም አገልግሎት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሐይቁ ላይ አረሙ በመከሰቱ  ጥቅማቸውን በመጋፋት መቸገራቸውን አመልክተው አሁን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን አረሙን በሰው ጉልበት የማስወገድ ስራ መጀመራቸውን  ተናግረዋል፡፡

በመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብር ወደ አካባቢው ከመምጣታቸው በፊት ለከብቶቻቸው ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ቶች ጋች ናቸው፡፡

ወደዚህ ከመጡ በኋላ ግን ሐይቁ በመኖሩ ቋሚ ኑሮ መጀመራቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ በሐይቁ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ጉዳት እያደረሰ ስጋት ሆኖባቸው የማስወገድ ስራ ላይ መሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡

" በቀጣይም የጀመሩትን የእምቦጭ አረም የማስወገድ ሥራ በማጠናከር ሐይቁን ሙሉ በሙሉ ከችግሩ ለማውጣት እንሰራልን" ብለዋል፡፡

የኢታንግ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ማኑቺ በበኩላቸው የእምቦጭ አረም በሐይቁ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመከናወኑ  ህብረተሰቡ በተነሳሽነት  የማስወገዱን ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከአካባቢው አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ጋር በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃውን ሥራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡

የአምቦጭ አረም ከዚህ በፊትም በጣና ሃይቅና በአባይ ወንዝ ላይ እንዲሁም በአርባ ምንጭ አከባቢ የውሃ አካላት ላይ ተስፋፍቶ የመከላከሉ   ስራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተካሄደ መሆኑን ቀደም ሲል ኢዜአ በተከታታይ ሲዘግብ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም