በምሥራቅ ወለጋ እና ሰሜን ሸዋ ከ158ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው

72

ነቀምቴ ጥር/ ፍቼ 7/2011 በምሥራቅ ወለጋ  እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች በተያዘው የበጋ ወራት ከ158ሺህ 600  ሄክታር በላይ  መሬት በመስኖ እየለማ ነው፡፡

በምሥራቅ  ወለጋ  በዞን  የመስኖ ልማት ባለ ሥልጣን የመስኖ ግብርና ኤክስቴንሽን የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አብዱ ኢፋ እንዳሉት እየለማ ያለው በመጀመሪያው ዙር  በ17 ወረዳዎች ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ነው፡፡

ይህም በዚሁ ዙር 95 ሺህ 283 ሄክታር ለመሸፈን ከታቀደው ውስጥ ነው።

ልማቱ  ባህላዊ፣ ዘመናዊ፣የውሃ መሣቢያ ሞተርና የጉድጓድ ውሃ  በመጠቀም ነው የሚከናወነው ።

ድንች፣በቆሎ፣ሽንኩርት፣ቀይ ሥር፣ቲማቲም፣ጥቅል ጎመን፣የአበሻ ጎመን፣ቃሪያና አንጮቴ በዞኑ በመስኖ እየለማ ካለው ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ከ113 ሺህ  በላይ  አርሶ አደሮች በልማቱ እየተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም  ከ10 ሺህ የሚበልጡት ሴቶች ናቸው፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ከ13 ሚሊዮን   ኩንታል በላይ  ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

በመስኖ ልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል በጊዳ አያና ወረዳ የአንገር ጉቴ ቀበሌ ሁለት ነዋሪ አቶ  ከድር ሱሌማን በሰጡት አስተያየት የእርሻ መሬታቸውን በአበሻ  ጎመን፣ቃሪያ፣ሙዝና ሸንኮራ አገዳ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመስኖ ሥራ ከጀመሩ 12 ዓመታት እንደሆናቸው  አስታውሰው የውሃ መሣቢያ ሞተር በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያመርቱ ገልጸዋል።

ከመስኖ ልማቱ ባገኙት ገቢ ከሣር ቤት ወጥተው ሁለት የቆርቆሮ መኖሪያ ቤቶችን መስራታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ 50 ሺህ ብር በባንክ መቆጠባቸውንም አስረድተዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ አርሶ አድር ተገኝ ይመር በበኩላቸው በ2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የውሃ መሣቢያ ሞተርን በመጠቀም የተለያዩ አትክልቶችና  ሙዝ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ከቃሪያና ቲማቲም ሽያጭ  50 ሺህ ብር ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመወ ከሙዝ ሽያጭ  በዓመት በአማካይ 70 ሺህ ብር እንደሚያገኙ ካለፈው ተሞክሯቸው በመነሳት ገልጸዋል፡፡

 በሚያከናውኑት ልማት ሶስተ የእህል መጋዘኖችን ገንብተው በማከራየት ላይ መሆናቸውንና በአዲስ አበባ ከተማ መኖሪያ ቤት መግዛታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶአደሮች በገበያ ተኮር ምርቶች ላይ በመስራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር ቶልቻ  አመንቴ በያያጉለሌ ወረዳ  የአቡ ይፈም ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  በተያዘው የበጋ ወቅት  ገበያ ተኮር ሰብሎችን በማልማት ላይ እንደሚገኙ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት ከልማቱ የሚየገኙት ገቢ እስከ ሶስት መቶ ሺህ ብር መድረሱን  የጠቆሙት አርሶ አደሩ በዓመት ከመስኖ ምርት  ሽያጭ እስከ 8ዐ ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ አመልክተዋል፡፡

የመስኖ እርሻቸውን በሞተር በመታገዝ በማከናወን ላይ ያሉት የግራር ጃርሶ ወረዳ የስልሚ ገጃባ  ቀበሌ አርሶ አደር አቶ  መኩሪያ  ዝናቡ  በበኩላቸው  ባለፈው ዓመት በአንድ ዙር የአትክለትና ፍራፍሬ ሽያጭ 77 ሺህ ብር ገቢ መግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ምትኩ በ13 ወረዳዎች 141 ሺህ አርሶ አደሮች በመስኖ ስራው እየተሳተፉ ነው፡፡

በተያዘው ዓመት  86 ሺህ 688 ሄክታር መሬት በባህላዊና ዘመናዊ  የመስኖ እርሻ በመጀመሪያ ዙር  መሸፈኑን  አመልክተው “ ሁለተኛ ዙር ሲታከልበት 121 ሺህ ሄክታር መሬት ይደርሳል” ብለዋል ፡፡

አቶ ተስፋዬ  እንዳሉት ለመስኖ ልማቱ ዘጠኝ መካከለኛ ግድቦችን ጨምሮ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የተጠለፉ 71 ወራጅ ወንዞች ፣ የከርሰ ምድር ውሃና ጉድጓዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም