ኢትዮጵያ በ2019 በአፍሪካ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ 10 ሀገራት አንዷ ሆነች

70

ጥር 7/2011 በአዲሱ የጎርጎሮሳውያን አመት በአፍሪካ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ተመራጭ ከሆኑ አስር ምርጥ ሃገራት ኢትዮዽያ አንዷ መሆኗን ቬንቸርስ አፍሪካ የተሰኘው ድረ ገፅ ዘግቧል።

በሃገሪቱ የተፈጠረውን የቢዝነስ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚያስችል ጊዜው አሁን መሆኑን የጠቀሰው ድረ ገፁ በኢትዮዽያ አለም እየመሰከረለት ያለውና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማሻሻል እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እርምጃ ዋቢ አድርጓል።

ዘ ራንድ መርቻንት ባንክ( RMD) የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ የፋይናንስ ተቋም ያወጣውን ሪፖርት መሰረት ያደረገው መረጃው የአህጉሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ምልከታን በመመርኮዝ አስሩ አገራት ኢንቨስት ለማድረግ የተመቹ መሆናቸውን አስነብቧል።

ከአለም በህዝብ ቁጥሯ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አህጉረ አፍሪካ በዕድገትና በልማት ረገድ ታላቅ ግስጋሴ እያደረገች እንደሆነ የጠቀሰው ድረ ገፁ መንግስታቶቿም ቀስ በቀስ ብዝሃነት ትርጉም ላለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደሚያበቃ እየተረዱት እንደመጡ ፅፏል።

ድረ ገፁ በተያዘው የፈረንጆች አመት መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ አስሩ ምርጥ ሃገራት ካላቸው ውስጥ ሃገራችንን ጨምሮ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና እና አይቮሪኮስት ይገኙበታል።

በተናጠል የሚደረግ እንቅስቃሴ ለመለወጥ እንደማይበጅና መዋቅራዊ ለውጥና የግል ባለሃብቶች ታላቅ ተሳትፎ የአፍሪካን እምቅ አቅም ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑን ድረ ገፁ በዘገባው አካቷል።

ምንጭ፡ሴንቸርስ አፍሪካ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም