የክፍለ ጦሩ አባላት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ

86
ጋምቤላ ግንቦት 18/2010 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሀገር መከላከያ ስራዊት የ12ኛው ክፍለ ጦር አባላት ገለጹ። በሀገር አቀፍ ደረጃ በየክፍለ ጦሩ እየተዘዋወረ ያለው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ትናንት ጋምቤላ ከተማ ሲደርስ የክፍለ ጦሩ አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል። በአቀባበል ስነ- ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክፍለ ጦሩ አባላት በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ከአባላቱ መካከል አስር አለቃ ጥሩጎበዝ ደጀኔ በሰጡት አስታየየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የኢትየጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ትልቅ ሀብት ነው። ሰለሆነም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ  በስጦታም ሆነ ቦንድ ግዥ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ለግድቡ ግንባታ የሰባት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን የገለጹት ደግሞ ወታደር መሰረት መገዜ ናቸው ። ሌላው አስተያየት ሰጪ አስር አለቃ በየነ ይልማ በበኩለቸው ’’የህዳሴው ግድብ የአንድነታችን አርማ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ  ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ’’ ብለዋል። ’’ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አይደልም ገንዘብ ህይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ’’ ያሉት  ደግሞ ምክትል አስር አለቃ ብሬ ከላይ ናቸው። በምዕራብ ዕዝ የ12ኛ መተማ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ኮርኔል ምሩጽ ወልደገብሬል እንደሚሉት ’’የህዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ የእድገት መሰረት የሚሆን ብቻ ሳይሆን በህዝብ ተሳትፎ የተገነባ ስለሆነ የኩራት አርማችን ነው ’’ ብለዋል። በመሆኑም ሰርዓቱ የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ በለፈ የግድቡ ግንባታ ፍፃሜውን እንዲያገኝ የሰራዊቱ አባላት በየዓመቱ በአንድ ወር ደመወዛቸው የቦንድ ግዥ እያካሄዱ እንደሚገኙና በቀጠይም ይኸው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም የዋንጫውን መምጣት በማስመልከት የክፍለ ጦሩ አባላት የቦንድ ግዥ እያካሄዱ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰናይ አኩዎር በአቀባበል ስነ- ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የሀገር መከላከያ ስራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬት እያደረገ ያለውን ድጋፍ የሚደነቅ ነው ። በአሁኑ ወቅትም ለግድቡ ግንባታ ማስፈጸሚያ ስራዊቱ እያደረገ ላለው ጥረት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም