ማዕከሉ በነፃ እየተደረገልን ያለው የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ተጠቃሚ አድርጎናል-የማዕከሉ ተገልጋዮች

94

ባህርዳር ጥር 6/2011 በባህር ዳር አካል ተሃድሶ ማዕከል የተደረገላቸው የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ  ሥራቸውን ለማከናወን እንዳገዛቸው የማዕከሉ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡

አካል ጉዳተኞች ወደ ማዕከሉ ባለመምጣታቸው ማዕከሉ በአቅሙ ልክ እየሰራ እንዳልሆነም  አመልክቷል።

በማዕከሉ አንዳንድ ተገልጋዮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በማዕከሉ በነፃ እየተደረገላቸው ያለው የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ  የዕለት ከዕለት ስራቸውን ለማከናወን አግዟቸዋል፡፡

ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ በመኪና አደጋ ምክንያት አንድ እግራቸውን አጥተው ወደ ማዕከሉ የመጡት ልጅ አዲስ ወርቄ  እንደተናገሩት ሰው ሰራሽ እግር ተገጥሞላቸው ለመራመድ ልምምድ እያደረጉ ነው፡፡

አደጋው ከደረሰባቸው ዕለት ጀምሮ ተንቀሳቀሰው ለመሥራትና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲቸገሩ አንደነበር ገልጸዋል።

በማዕከሉ በተገጠመላቸው ሰው ሰራሽ እግር ለመራመድና ወደ ቤታቸው ተመልሰው በግብርና ሥራቸው ቤተሰባቸውን ለማገዝ ያስችለኛል የሚል ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።

ከክፍያ ነፃ የሰው ሰራሽ እግር ተገጥሞላቸው እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ደስታ እንደፈጠረባቸው የሚናገሩት ልጅ አዲስ፣ በቀጣይም በአካባቢያቸው መሰል ችግር ያለባቸውና በመረጃ እጥረት አገልግሎቱን ያላገኙ ሰዎችን ወደ ማዕከሉ እንደሚልኩ አስረድተዋል።

ከምስራቅ  ጎጃም ዞን አማኑኤል ወረዳ የመጡት ቄስ  ምንውየለት አማኑ በበኩላቸው በሚስማር ሳቢያ በተከሰተው በሽታ አንድ እግራቸው የተቆረጠው ከስድስት ወራት በፊት እንደነበር ያስታውሳሉ።

በማዕከሉ የተገጠመላቸው ሰው ሰራሽ እግር እንደተፈጥሮ እግር መራመድ አስችሎኛል ብለዋል፡፡

ይህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማከናወን እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል።

የባህር ዳር አካል ተሃድድሶ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ በላይነሽ ታፈረ በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ብዛት በትክክል ባለመታወቁና ለአካል ጉዳተኞች መረጃ ባለመድረሱ ማዕከሉ መሥራት ያለበትን ያህል በመሥራት ላይ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ማዕከሉ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበርና ከአማራ ክልል መንግሥት በሚመድብለት በጀት ሰው ሰራሽ አካልና ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ መሣሪያዎችን እያመረተ ለአካል ጉዳተኞች በነፃ ድጋፍ ያደርጋል።

የድሃ ድሃ ለሆኑ የአካል ጉዳተኞችም የትራንስፖርት ወጭን ጭምር እንደሚሸፍንም ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል።

የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ  ቢሮ የተደራጀ የአካል ጉዳተኛች መረጃ ባለማቅረቡ ማዕከሉ የሚጠበቅበትን ያህል መሥራት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ባለፉት 13 ዓመታት ከ26 ሺህ ለሚበልጡ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዊ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አበጀ በበጀት እጥረት አደረጃጀቱ እስከ ዞን ድረስ ብቻ በመሆኑ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር መለየትና ግንዛቤ ለመፍጠር አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የቢሮውን መዋቅር እስከ ወረዳና ቀበሌ በማስፋት የአካል ጉዳተኞች መጠንና የአካል ጉዳት ዓይነቶችን ለመለየት የክልሉ መንግሥት በጀት እንዲመድብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የባህር ዳር አካል ተሃድሶ ማዕከል በ1997 በተለያዩ ምክንያቶች ለአካል ጉዳተኝነት የተጋለጡ ሰዎችን የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ እንዲሰጥ የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም