በሲዳማ ዞን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መግባባት ላይ ተደረሰ

93

ሀዋሳ ጥር 6/2011 የሲዳማ ወጣቶች የጠሩት የአፊኒ ሥነ ሥርዓት በሀዋሳ ከተማና በዞኑ ከተሞች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ በመድረስ ተጠናቀቀ፡፡

በወጣቶቹ የተዘጋጀው መድረክ የዞኑ የአገር ሽማግሌዎችና አመራሮች በተገኙበት ትናንት በከተማዋ ተካሂዷል፡፡

የሲዳማ ባህላዊ ሥርዓት በሚካሄድበት ሶሬሳ ጉዱማሌ ፓርክ በተካሄደው ውይይት ወጣቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ በዞኑ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ተቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል።

ወጣቶቹን በዞኑ እያደረጉት ያለውን አስመልክቶ በማህበራዊ ድረ ገጾችና በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በከተማዋና አካባቢው ሰላም እንደሌለ ተደርጎ የ7ሚሰራጨው መረጃ ትክክል እንዳልሆነም ተገልጿል ፡፡

የሲዳማ ዞን ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ያምሮት ኃይሌ እንዳሉት ለዘመናት በሲዳማ ህዝብ ሲጠየቅ የነበረው የክልል ጥያቄን በማስቀጠል ኤጀቶዎች እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ ከብጥብጥ ጋር ተያይዞ መነሳቱ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል።

ከሲዳማ ወጣቶች መካከል ታሪኩ ለማ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄን ታፍኖ መቆየቱን አስታውሶ፣በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወጣቶቹ ክልል ለመሆን ጥያቄውን ከዞኑ ሕዝብ ጋር ማንሳታቸውን ገልጿል።

ኤጀቶዎች የህዝቡን ጥያቄ ለማሰማት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ፀረ ሕዝብ አድርጎ ሲፈረጁ እንደሚታይ የገለጸው ወጣቱ፣ ይህም በሀዋሳና ሌሎች አንዳንድ የዞኑ ከተሞች በሚኖረው ህዝቡ ላይ ስጋት ማሳደሩን ተናግሯል።

የሶስተኛ ዲግሪ የሥነ ልሳን ተማሪው ሳሙኤል በላይነህ በበኩሉ ኤጀቶዎች በሀዋሳና በሲዳማ ዞን ሕዝብ  ላይ እንደተነሳ ተደርጎ ለዘመናት በጋራና በአንድነት የሲዳማን ባህልና ሥርዓት ተቀብሎ የሚኖረውን ሕዝብ ስጋት ላይ መጣል ሁኔታ ተገቢ አይደለም ብሏል።

የወጣቶችን እንቅስቃሴ የዞኑ የአገር ሽማግሌዎች ያልተቀበሉ ተደርጎ መውሰድ ተገቢ እንደማይሆን ተናግሯል፡፡

በውይይቱ ከተካፈሉት የአገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ዓለሙ አደመ ውይይቱ ችግሮች በቀጣይ እንዳይፈጠሩና በሕዝቡ መካከል ያለውን አብሮነት ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲያስ "አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሁሉም መደማመጥ እንዳለበት በመረዳት ይህ የአፊኒ/የእንደማመጥ/ ውይይት መድረክ በወጣቶቹ ተዘጋጅቷል" ብለዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለማለፍ ውይይቱ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ ውይይቱ በሀዋሳ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎች በሚዘጋጁ መድረኮች እንደሚቀል ተናግረዋል።

በኤጀቶዎች፣በአገር ሽማግሌዎችና በአመራሩ ዘንድ በሰላም ዙሪያ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የህዝብን ጥያቄ መነሻ አድርገው የሚታዩ አዝማሚያዎች መታረም እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በሲዳማ ብሔር ዘንድ "አፊኒ" ማለት እንደማመጥ ማለት ነው። የተለያዩ ጉዳዮች በአገር ሽማግሌዎች ዳኝነት ሁሉም አካላት ተነጋግረውና ተደማምጠው ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ሥርዓት ነው።

በአገራዊና በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመከረው መድረክ ላይ ከዞኑ ከ30 በላይ ወረዳዎችና ከሀዋሳ ከተማ የተውጣጡ ወጣቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም