በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የተከሰተው ግጭት ወደ መረጋጋት እየተመለሰ ነው…የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

1083

ባህርዳር ጥር 6/2011 በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የተከሰተውን ግጭት በጸጥታ አካላትና ህብረሰቡን ባሳተፈ ጥረት ወደ መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈር ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አሰማሃኝ አስረስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሰሞኑን በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋት ችግር ተከስቶ መሰንበቱን አስታውሰዋል።

በተለይም በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስና አካባቢው በአማራና ቅማንት ማህበረሰብ በተከሰተው ግጭት የህይወት መጥፋት ፣የአካልና የንብረት ውድመት መድረሱን ተናግረዋል።

በወንድማማች ህዝቦች መካከል በተከሰተው ግጭትና በደረሰው ጉዳትም የክልሉ መንግስት ማዘኑን ጠቅሰው፤ እየተከናወኑ ባሉ አካባቢውን የማረጋጋት ሥራዎች አንፃራዊ ሰላም መስፈን መጀመሩን ገልፀዋል።

የመከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር፣የሃገር ሽማግሌዎችና ማህበረሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው ከግጭቱ ጀርባ የሚያደራጁ፣ስልጠናና መሳሪያ የሚሰጡ አካላት እንዳሉበት መታየቱንም ኃላፊው ተናግረዋል።

በግጭቱ የሚሳተፉ አካላትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበው፤ “የግጭቱን ምንጭ የሚያጣራ ግብር ሃይልም ወደ ቦታው ተልኮ የማጣራት ስራ እያከናወነ ነው” ብለዋል።

በግጭቱ እጃቸው ያለበት አካላትም በቀጣይ ተጣርተው ለህግ እንደሚቀርቡ ጠቅሰው ህብረሰተቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን ሆኖ የጀመረውን ድጋፍና እገዛም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እያደረገ ሲሆን የሰራዊቱን ስም እያጠፉ ከህዝብ እንዲነጠል የሚሰሩ አካላት እንዳሉም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተፈናቅለው የመጡ ተማሪዎች የክልሉ መንግስት የምግብና ጊዜያዊ መጠለያ መሰጠቱን የገለፁት አቶ አሰማሃኝ “ጉዳዩን የፌደራል መንግስትን የሚመለከተው በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ከጊዜያዊ ማረፊያቸው እየወጡ የባህር ዳር ከተማን ለመበጥበጥ የሚሞክሩ አንዳንድ ተማሪዎች ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመው፤ ምላሽ እስኪሰጣቸውም መረጋጋትና በትዕግስት ሊጠብቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአማራና የትግራይ ክልሎች የስፖርት ቡድኖች በሜዳቸው እንዲጫወቱ ሲደረግ የነበረው ጥረት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑንም ገልጸው “ለዚህም የሁለቱ ክልልች አመራሮች፣ ስፖርተኞች፣ የደጋፊ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል”ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በአጭር የሞባይል መልዕክት/SMS/ የትራንስፖርት መመሪያ ሊተገበር ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ ተፈጥሮ የነበረው የትራንስፖርት መስተጓጎልም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት መፈታቱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ለማድረግ ሁሉም በባለቤትነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አቶ አሰማሃኝ አቶ አሰማኸኝ አሳስበዋል።