ኢትዮጵያና ሱዳን የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ተስማሙ

100
ሱዳን ሚያዝያ 25/2010 ኢትዮጵያና ሱዳን የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ተስማሙ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የዶክተር አቢይ አህመድን የሱዳን ጉብኝት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጎረቤት አገራት በሰጠው ትኩረት መሰረት ባለፉት ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል። በአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን ጉብኝትም ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን  ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር በዋናነት በአራት ጉዳዮች ላይ የተስማሙ ሲሆን ይህም የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ከግምት ያስገባ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም መሰረት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን የህዳሴ ግደብ በተለይም የተፈጥሮ መብትን ባከበረና የሌላውን ጥቅም በማይነካ መልኩ ለማስቀጠል ተስማምተዋል። በሱዳን በተለያየ ምክንያት በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን ጥያቄም ፕሬዝዳንት አልበሽር ተቀበለው፤ ለመፍታት ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል። የድንበር ልማትን በተመለከተ አሶሳን የድንበር ከተማ ለማድረግና በተጨማሪም አገራቱን በባቡር መስመር ለማስተሳሰር የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ነው የጠቆሙት። በተለይም  ከፊል የሱዳን ወደብን በጋራ የማልማትና ለማስተዳደር መስማማታቸውን አስረድተዋል።
ትላንት በሁለቱ መሪዎቹ መካከል በተደረገ ውይይት  ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን በሼር ሆልደርነት እንድታለማ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ፤ ይህም አዲስ ሃሳብ ነው፤ ስለዚህ በርካታ አዳዲስ ውሳኔዎች የተወሰኑበት፤ የፖለቲካ ግንኙነታችንን የበለጠ ያጠናከርንበት፤ የኢኮኖሚ ግንኙነታቸንም በተለይም የኢኮኖሚ ውህደታችንን የበለጠ የሚያጠናክሩ በርካታ ውሳኔዎች የተወሰኑበት፤ በጣም በወንድማማችነት መንፈስ የሁለቱን አገሮች ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የተደረገ ውይይትና ውሳኔ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በአገራቱ መሪዎች የተደረሱት የልማትና የፖለቲካ የትብብር መስኮች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ክትትል በማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ሚኒስትሩ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአገራዊ የውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ እያደረገች ያለውን አዎንታዊ ፖለቲካዊ ለውጦች ፕሬዝዳንት አልበሽር “አስደስቶኛል” ብለው መናገራቸውንም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት እንደምታደርገው በቀጠናዊና በአህጉራዊ ጉዳይ ላይ ያላትን ተሰሚነትና የመሪነት ሚና አጠናክራ እያስቀጠለች መሆኑን መታዘባቸውንም እንዲሁ። የኢትዮጵያና የሱዳን ታሪካዊ ግንኙነት ከቀደምት የሥልጣኔ ዓመታት ጀምሮ እስከአሁኑ ዘመናዊው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም