የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለጎረቤት አገሮች የሚፈለገውን ትኩረት የሰጠ አይደለም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

126

አዲስ አበባ ጥር 6/2011የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለጎረቤት አገሮች የሚፈለገውን ትኩረት የሰጠ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ፖሊሲው ወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በሚመጥን መልኩ እንደገና እየተሻሻለ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  "ዓለም ዓቀፍ አዝማሚያዎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ" በሚል ርዕስ  በኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች ገለጻ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፖሊሲው ሲረቅ የነበሩ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ዛሬ ላይ ተቀይረዋል።

ፖሊሲው "ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት በመሆኑም ለውስጥዊ ጥንካሬና ለአገራዊ ህልውና የሰጠው ትኩረት የሚበረታታና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በአገራት ውስጣዊ ሁኔታ አለመግባት እንዲሁም ከውግንና ይልቅ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም መቆሙም በጥንካሬነት የሚነሳ መሆኑንም አውስተዋል።

ይሁን እንጂ ፖሊሲው "ለጎረቤት አገሮች የሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ጎረቤት አገሮችን ዘሎ ከየትኛውም አገር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ደግሞ ውጤታማ እንደማይሆን አብራርተዋል።

ፖሊሲው ላይ የተቀመጡ ግቦችም "ግልጽና በየጊዜው የሚለኩ አይደሉም" ነው ያሉት።

ተወደደም ተጠላም ከሉላዊነት ተጽዕኖ ማመልጥ እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ፖሊሲው ይህንን ጉዳይ ለማስረዳት የማያስፈልጉ ሀተታዎችን አካቷል ብለዋል።

በቀጣይ በሚሻሻለው ፖሊሲ ላይ የሉላዊነት ጉዳይ እንደማይካተት በመጠቆም።

በተጨማሪም ፖሊሲው አንድ ላይ ሊሄዱ የማይችሉ የውጭ ግንኙነትና የአገራዊ ደህንነት ጉዳዮችን አጣምሮ መያዙ አግባብ አለመሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ አንስተዋል።

ዛሬ ላይ ስጋት የሆኑ ማናቸውም ጉዳዮች በቅጽበት ሊቀየሩ ስለሚችሉም  በየጊዜው ሊሻሻል የሚችል እራሱን የቻለ አገራዊ የደህንነት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ፖሊሲው ሲቀረጽ ያልነበሩና አሁን ላይ እየተስፋፉ የመጡት የማህበራዊ ሚዲያና ሳይበር ቴክኖሎጂ በውጭ ግንኙነቱ ላይ የሚኖረው ጥቅምና ስጋትም በማሻሻያው ላይ እንደሚካተትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ገቢራዊ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም