በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጋራ እሴት በመላላቱ የማንነት ግጭቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል - ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ

80

አዲስ አበባ ጥር 6/2011 በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ስርዓት የጋራ እሴት በመላላቱ የማንነት ግጭቶች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ ገለጹ።

ማንነትን መሰረት በማድረግ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጡ ህጎችና ፖሊሲዎች ሊኖሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሰላም ሚኒስቴር "የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገራዊ ሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ከመላ ሀገሪቱ ከተውጣጡ 1 ሺህ 200 ከሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር  ዛሬ መክሯል።

ዓለም አቀፍ የእርቅና ሰላም አደራዳሪና መምህር ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ ባቀረቡት የመነሻ ፅሁፍ፤ "ብሄርን፣ ጎሳንና ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት ጉዳቱ ከሁሉም የከፋ ነው"።

በኢትዮጵያ ላለው ወቅታዊ አለመረጋጋትና ግጭት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ቢኖሩም "በማንነት ሳቢያ የሚከሰተው ግን ከሁሉም ይልቃል" ብለዋል።

በመሆኑም አንድነትን በማላላት ብሄርን ትኩረት ያደረገው የፖለቲካ ስርዓት ተፈትሾ ከብሄር ይልቅ የጋራ እሴትን መሰረት ያደረገ አካሄድ መጠናከር ይኖርበታል ብለዋል።

የዜጎች ዲሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መልኩ መከበርና ሁሌም ዜጎች በህግ ፊት እኩል የሚዳኙበት ስርዓት መፈጠር እንዳለበትም ተናግረዋል።

የማንነት ግጭት ደግሞ እንደ እሳት እተቀጣጠለ እንደ ወረርሽኝ ከሰው ወደ ሰው እየተዛመተ የሚሄድ አደገኛ ችግር በመሆኑ የሚያመጣው ቀውስ የከፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በመሆኑም የዜጎች የባህልና የማንነት ልዩነቶች ጌጥ መሆናቸውን በአዎንታዊ ጎኑ በመረዳት ዜጋ አንደመሆናቸው ፍትሃዊና እኩል አገልግሎት መስጠት ይገባልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የብሄሮች የባህል ጥናት በባህላቸው መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ ማውጣት እንጂ እንደ አንድ ሀገር ዜጎች በመካከላቸው ያለውን አንድነትና ተዛምዶ አያሳይም ብለዋል።

"ብሄር ላይ ማተኮሩ ስህተት አይደለም" ያሉት ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ፤ "የእኔን ማንነት የሚገልጸው ብሄሬ ብቻ ነው ማለት ግን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያስተሳስር ማንነት እንዳለ መዘንጋት ነው" ብለዋል።

ማንነትን መሰረተ ያደረገ ግጭት የሚያስከትለውን አደጋ ከሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መማር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ማንነትን መሰረት በማድረግ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጡ ህጎችና ፖሊሲዎችን መተግበር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገድ ለእርቅና ለሰላም ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የሀገር ሽማግሌዎችን መደገፍና ማክበር ይኖርበታልም ብለዋል።

በተጨማሪም የወጣቶችም ባህላዊ እሴት በአውሮፓውያን ባህል እየተሸረሸረ መምጣቱን ገልጸው፤ ወጣቶች ችግሮችን በሰከነ መንገድ መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይበጠስና ድልድዩ እንዳይፈርስ የሀገር ሽማግለዎች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባትና ህግ የሚከበርባት አገር እንድትሆንም የሀገር ሽማግሌዎች በራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና እውቀት ስለሰላም እንዲሰብኩና ስሰላም በትጋት መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም