ባለሃብቶቹ የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

82

ጋምቤላ ጥር 6/2011በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ።

 የክልሉ መንግሥት ለባለሃብቶቹ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ርዕስ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ባለሃብቶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በክልሉ መሬት ተረክበው ወደ ልማት ቢገቡም፤ የመሠረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የገበያ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በኢታንግ ልዩ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሃብቶች መካከል አቶ እርጥቤ ቢያድግልኝ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመዘርጋቱ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የሚመለከተው አካል ችግሩን እንዲፈታላቸው ባለሀብቱ ጠይቀዋል።

መሬቱ በማልማት ትርፋማ መሆን ሲጀምሩ ድንብር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮች ችግር እያደረሱባቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ ባለሃብት አቶ ማለፊያ ማሞ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ምርታቸውን ወደ ገበያ በሚወስዱበት ወቅት ተገቢ ያልሆነ የኬላ ቀረጥ ለመክፈል መገደዳቸውንም ተናግረዋል።

  ሌለው ባለሃብት አቶ ተስፋ እደግልኝ እንዳሉት በመንገድ ችግርና በፈላታ አርብቶ አደሮች የጸጥታ ስጋት ወደ እርሻ ቦታቸው የሚሄድ ሠራተኛ በማጣታቸው ሰብላቸውን ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአበቦ ወረዳ የሳኡዲ ስታር የእርሻ ልማት ኩባንያ ተወካይ አቶ አብዲሳ ቹቹ በበኩላቸው ኩባንያው በአካባቢው ሥራን ከመፍጠር ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ኩባንያው ለሚያለማው የሩዝ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በኤሌክትሪክ እጦት ማምረት እንዳልጀመረ ገልጸዋል።

የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ የጥጥ፣ የማሾ፣ የሰሊጥና ሌሎች ምርቶቻቸውን በወረደ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን የገለጹት ደግሞ በጋምቤላ ወረዳ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ተሰፋዬ አሻግሬ ናቸው።

እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በዘርፉ የተሰማራውን ባለሃብት በጅምላ ከመፈረጅ ወደ ልማት ያልገቡትን በመለየት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በሰጡት ምላሽ ባለሃብቶች ያቀረቧቸው የኤሌክትሪክ ፣ የመንገድና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ጥያቄች እግባብነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከመልካም አስተዳደርና ከድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች ጋር ተያይዞ የቀረቡትን ቅሬታዎች ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም  አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግሥት አልሚ ባለሃብቶች ያሉባቸውን ችግሮች እንደሚፈታና ድጋፍ  እንደሚያደርግ  አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ መሬት ተረክበው ወደ ልማት ያልገቡ ባለሃብቶችን በመለየት እርምጃ እንደሚወስድ ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

በጋምቤላ ክልል ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄከታር መሬት ከተረከቡት ከ700  በላይ ባለሃብቶች ወደ ሥራ የገቡት ገሚሱ ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም