ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው በሽሬእንዳስላሴ ለሚገነባው ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

151

ሽሬ እንዳስላሴ  ጥር 6/2011 ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ዛሬ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ለሚገነባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ቀዳማዊት እመቤቷ እንደተናገሩት የሚገነባው ትምህርት ቤት በተለያዩ ክልሎች ከሚገነቡት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው።

የሃገሪቱ ልማት በታቀደው መልኩ ሊቀጥል የሚችለው በሁሉም ስፍራ አስተማማኝ ሰላም ሲኖር መሆኑንም ወይዘሮ ዝናሽ በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ይሄንን አውቆ በእጁ ያለውን ሰላሙን እንዲንክባከብ ያሳሰቡት ቀዳማዊት እመቤቷ “በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ተገኝቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ለማኖር በመብቃቴ የተሰማኝ ደስታ ወሰን የለውም” ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በሽረ እንዳስላሴ ከተማ የመሰረተ ድንጋዩ የተቀመጠው የ2ኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ግንባታ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ በኢፌዴሪ ቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት እንደሚሸፈን ታውቋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ ግንባታው ተጠናቆ ተማሪ እንዲቀበል የከተማዋ ህዝብ የተለመደውን ድጋፉን ማበርክት ይጠበቅበታል ።

የከተማዋ የአገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ አረጋይ አየለ በበኩላቸው በከተማዋ ተጨማሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ቀዳማዊት እመቤቷ በአካል ተገኝተው የመሰረት ድንጋይ በማኖራቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ እስኪጠናቀቀም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚተጉ ተናግረዋል።

የሚገነባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለውና ዘመናዊ መሆኑንም የከተማዋ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሓዱሽ ሃይሌ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም