ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስፔን ቫሌንሺያ በተካሄደ የጎዳና ላይ ሩጫ አሸነፉ

75

አዲስ አበባ ጥር 6/2011 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሁለቱም ጾታዎች አሸንፈዋል።

በሴቶች በተካሄደው ውድድር አትሌት ጸሐይ ገመቹ በ30 ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ  የግል ምርጥ ሰአቷን በማስመዝገብ አሸናፊ ሆናለች።

ኬንያዊቷ ግሎሪያ ኪት 30 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ  በመግባት ሁለተኛ የወጣች ሲሆን ሁለቱ አትሌቶች እስከ ውድድሩ ማብቂያ ድረስ ጠንካራና አስገራሚ ፉክክር እንዳደረጉ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።

ሌላኛዋ ኬንያዊ ኢቫሊን ቺርቺር 30 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ጫላ ረጋሳ  27 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ በመግባት የቦታውን ክብረ ወሰን በ29 ሴኮንድ በማሻሻል አሸናፊ ሆኗል።

ዩጋንዳዊው ስቴፈን ኪሳ በአንድ ሴኮንድ ዝቅ ብሎ 27 ደቂቃ ከ24 ሴኮንድ ሁለተኛ ሲሆን ኬንያዊው ቬዲች ቼሮይት 27 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በወንዶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁት አትሌቶች የገቡበት ሰዓት ተቀራራቢ መሆን እስከ ውድድሩ መጨረሻ ብርቱ ፉክክር እንዳደረጉ የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያውያኖቹ አትሌቶች ባትሰፋ ጌታሁንና አባይነህ ደጉ በቅደም ተከተል አራተኛና ሰባተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በውድድሩ ሰአት የነበረው የአየር ምጣኔ 6 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደነበረና ይህም ከተጠበቀው በላይ ቅዝቃዜ እንደነበር ተገልጿል።

በስፔን ቫሌንሺያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የጎዳና ሩጫ ዘርፍ የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

በሌላ በኩል ትናንት በስፔን ኤልጎይባር በተካሄደ የሁዋን ሙዌርዛ የአገር አቋራጭ ውድድር በወንዶች የ10 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ 32 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥቷል።

ኬንያዊው የ19 ዓመት ታዳጊ ሮኔክስ ኪፕሩቶ 32 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን ሌላኛው ኬንያዊ ስታንሊ ዌይትሀካ 32 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ሶሰትኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

አትሌት ሰለሞን የባለፈው ዓመት አሸናፊነቱን ያስጠብቃል የሚለው ግምት ሳይሳካ ቀርቷል።

በሴቶች የ7 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቢሪ 24 ደቂቃ ከ 39 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን ዩጋንዳዊቷ ስቴላ ቼሳንግ 24 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ሁለተኛ ሆና ውድድሩን ጨርሳለች።

ሌላኛዋ ኬንያዊ ቢትሪስ ቼፕኮኤች 25 ደቂቃ ከ16 ሶሰትኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በዓለም አቀፉ የእትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፈቃድ የሚካሄደው የሁዋን ሙዌርዛ የአገር አቋራጭ ውድድር ውድድሩ ለስፔናዊው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ሁዋን ሙዌርዛ መታሰቢያ የሚካሄድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም