የቮሊቦልና እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል

392

አዲስ አበባ ጥር 6/2011 የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሄደዋል።

በ4ኛው ሳምንት ጨዋታ ሙገር ከ ወላይታ ዲቻ ባደረጉት ጨዋታ የስፖርታዊ ግድፈት ባሳዩ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል።

በ5ኛ ሳምንት ከትናንት በስቲያ በተደረገ ጨዋታ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተጫውቶ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በሊጉ አዲስ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ እስካሁን ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ትናንት በአዲስ አበባ በተደረገ ሌላ ጨዋታ መከላከያ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙገር ሲሚንቶን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ከትናንት በስቲያ ሶዶ ላይ በተደረገ ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስ የአምናውን የሊጉን አሸናፊ ወላይታ ድቻ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን ውጤቱም ወላይታ ድቻ ከነበረው ወቅታዊ አቋም አንጻር ‘ያልተጠበቀ’ ተብሏል።

ትናንት በባህርዳር በተደረገ ጨዋታ ባለሜዳው ጣና ባህርዳር ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን አስተናግዶ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 ረትቷል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታ ሙገር ከ ወላይታ ዲቻ ባደረጉት ጨዋታ የስፖርታዊ ግድፈት ባሳዩ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

ሁለቱ ቡድኖች ታህሳስ 21 ቀን በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ የወላይታ ድቻ ምክትል አሰልጣኝ ጥበበ ሳሙኤል የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ከሜዳ የተሰናበተ በመሆኑ የ2 ጨዋታ ቅጣት ተላልፎበታል።

እንዲሁም የሙገር ሲሚንቶው አምበል ዳዊት ተገኝ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲነፋ ወደ ዕለቱ ዋና ዳኛ በመሄድ ለፀብ የተጋበዘ በመሆኑ የ5 ጨዋታ ዕገዳ እንደተጣለበት ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

በጨዋታው ወቅት ሁለቱም ቡድኖች 8 የማስጠንቀቂያ ካርድ ማየታቸው ይታወሳል።

ከሁለቱም ክለብ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ተጫዋቾችና አመራሮች የታዩ በመሆኑ በቀጣይ ጨዋታ መታረም የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አመልክቶ ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ በመግለጽ ክለቦች አብረውት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ በተመሳሳይ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂዷል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የአምና አሸናፊው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ድሬዳዋ ከተማ 43 ለ 18 በማሸነፍ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

ቅዳሜ በአዲስ አበባ በተደረገ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መከላከያን 29 ለ 22 ሲያሸንፍ ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደ ጨዋታ ፌዴራል ፖሊስ ከምባታ ዱራሜን 21 ለ 20 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ከትናንት በስቲያ የሊጉ አዲስ ተሳታፊ የሆነው ጎንደር ከተማ በሜዳው ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ባደረገው ጨዋታ 27 ለ 23 ተሸንፏል።

በክልል ከተማ ትናንት መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከቡታጅራ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የቡታጅራ ከተማ እጅ ኳስ ቡድን በጀት ማንቀሳቀስ አልቻልኩም በማለቱ ጨዋታው አለመካሄዱ ታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ ዛሬ በሚያደርገው ስብሰባ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 የእጅ ኳስ ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።