ከኦሮሚያ ክልል አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ90 በመቶ በላይ የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን አሟልተው አይሰሩም

60

አዳማ ጥር 5/2011 በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ90 በመቶ በላይ የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን እንደማያሟሉ የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

በባለስልጣኑ የአካባቢ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ በፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በማምረት ላይ ከሚገኙት አምራች ኢንዱስትሪዎች አብዛኛዎቹ የተቀመጠውን ደረጃውን አያሟሉም።

በአገሪቱ ካሉት አምራች ኢንዱስትሪዎች 54 በመቶ የሚሆኑት በክልሉ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው፣ በክልሉ ከኢንቨስትመንት ቦታ አሰጣጥ ጀምሮ የአካባቢ ሥነ ምህዳርና ጥበቃን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ልማት መከናወኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኢንቨስትመንት የተሰጣቸው መሬት የእርሻ ማሳዎች ከመሆኑ ባሻገር፤ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣የኬሚካሎች አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርዓት ሳይዘረጉ ወደ ምርት መግባታቸውን አስረድተዋል።

ፍሳሽ ቆሻሻዎች፣ኬሚካሎችና ተረፈ ምርቶች የሳይንሳዊ የክምችትና ማስወገጃ ቦታ ሳይኖራቸው ወደ ምርት መግባት በኢንዱስትሪዎቹ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን መረጋገጡን ኃላፊው ተናግረዋል።

በዋናነት የፍሳሽ ቆሻሻዎች አዋሽን ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ ወንዞች እየተለቀቁ አርሶ አደሩ በሚያመርተው ሰብልና እንስሳት ላይ ጉዳት ያስከትላሉ፤ለዜጎች ጤና ጠንቅ ሆነዋል ብለዋል።

የአካባቢው ኅብረተሰብ ለውሃ ወለድ፣ለቆዳና ካንሰር በሽታዎች መጋለጡን አቶ  ስንታየሁ አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታትና አምራች ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ወደ አካባቢ አየር ንብረት ለውጥ በካይ ጋሶች በመልቀቅ በኅብረተሰቡ አኗኗር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳደሩ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን፣ የቆዳ ፋብሪካዎች፣የአበባ እርሻ ልማት ድርጅቶችና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን አስታውቀዋል።

አብዛኛዎቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ፣የአደገኛ ኬሚካሎችና አያያዝና አስተዳደር ሥርዓት ሳይዘረጉ በቅድመ ሁኔታ ወደ ሥራ ማግባታቸው ለችግሩ መንስዔ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሕግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ መሃሪ ወንድማገኝ ናቸው።

ኮሚሽኑ በፌዴራል ደረጃ ያሉት 55 ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በክልሎች ባሉት ኢንዱስትሪዎች ላይ በተካሄደው ጥናት አብዛኛዎቹ ከደረጃ በታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የአበባ እርሻ ልማት ድርጅቶች ውስጥ ሶስቱ ብቻ የወጣላቸውን የአካባቢ ጥበቃ ህግ በከፊል ያሟሉ ናቸው ያሉት አቶ መሃሪ፣ 28 የሚሆኑት የኬሚካል አያያዝና አወጋገድ ያለባቸውን አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ የህግና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢውና ኅብረተሰቡ ጤና አመቺ እንዲሆኑ ከኢንቨስትመንት መሬት መረጣ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ የማስተካከያ እርምጃዎች ለመውሰድ በመሥራት ላይ ነን ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ፣የኬሚካል አጠቃቀምና አወጋገድ ዘመናዊ አሰራር እንዲከተሉ የክትትልና የቁጥጥር ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም