መከላከል በሚቻል በሽታ መሞት እንዲበቃ የህክምና ሙያ ምሩቃን ጠንክረው እንዲሰሩ ተጠየቀ

67

አዳማ ጥር 5/2011  የህክምና ሙያ ምሩቃን መከላከል በሚቻል በሽታ መሞት እንዲበቃ ጠንክረው እንዲሰሩ የሣይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ አሳሰቡ።

የአርሲ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 355 የጤና ባለሙያዎችን ዛሬ አስመርቋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳስገነዘቡት የህክምና ባለሙያዎች መከላከል በሚቻል በሽታ መሞት እንዲበቃ በመስራት ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሊረባረቡ ይገባል፡፡

በጤና አገልግሎትና አጠባበቅ ረገድ በሚታየው ውስንነት መዳን በሚቻልባቸው በሽታዎች ሰዎች እንደሚሞቱና ታክሞ መከላከል በሚቻል ሁኔታም የአልጋ ቁራኛ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራው ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከማፍራት አንፃር ትኩረት የሚሹ ቀሪ ሥራዎችን ለመፈጸም መሰራት እንዳለበት ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

የአርሲ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ኑዋማ ቢፋ ኮሌጁ ካስመረቃቸው መካከል 86ቱ የህክምና ዶክተሮች ናቸው።

ቀሪዎቹ በጤና መኮንን፣ክሊኒካል ነርሲንግ፣ሚድዋይፈሪና በሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ መስክ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መሰልጠናቸውን ጠቁመዋል።

በጤናው መስክ ሀገሪቱ ያለባትን  የባለሙያ እጥረት ለማቃለል ዩኒቨርሲቲው ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአርሲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ከህይወት ተሞክሯቸው ጋር በማዋሃድ በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነታውን  መወጣት እንዳለባቸውም  አሳስበዋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ  ዶክተር አዲሱ ነዲ በሰጠው አስተያየት በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ መሰረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከሴቶች ተማሪዎች በከፍተኛ ውጤት በማምጣት የተመረቀችው ዶክተር አያንቱ ሆርዶፋ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው የቀሰመችውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለውጥ ለማምጣት እንደምትጥር ተናግራለች፡፡

የህክምና ትምህርት የተግባር ትምህርት እንደመሆኑ እርስ በእርስ የነበረ የመማማር ሂደት አሁን ለደረሰችበት ስኬት እንደረዳት ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም